Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

ጥንት ከአባቶች የተረከብነውን የአብሮነት እሴት ጠብቆ ለማቆየት የሀይማኖት ተቋማት ሚና የጎላ ነው-ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር

ጥንት ከአባቶች የተረከብነውን የአብሮነት እሴት ጠብቆ ለማቆየት የሀይማኖት ተቋማት ሚና የጎላ መሆኑን የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር ገለፁ።

4ተኛው የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ “ሀይማኖቶች ለሰላም፣ለአንድነትና ለአብሮነት” በሚል መሪ ቃል በሀረር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር ጉባኤውን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለፁት ለሁሉም ነገር መሰረት የሆነውን ሰላም መጠበቅ ይገባል።

ሀረር የሀይማኖት ተቋማት እና ማህበረሰቡ ተከባብረው ለበርካታ ዓመታት አንዱ ለሌላው እንቅፋት ሳይሆን ድጋፍ በመሆን በአብሮነት የኖሩባት የሰላም ተሸላሚ ናት ።

ይህንን ከአባቶቻችን የተረከብነውን የሰላምና አብሮነት እሴት ጠብቀን ማቆየት ይገባል ብለዋል።

በተለይ ጥንት ከአባቶች የተረከብነውን የአብሮነት እና ሰላም እሴት ጠብቆ ለማቆየት የሀይማኖት አባቶችና ተቋማት ሚና የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።

ሰላም የሚጀምረው ከግለሰብ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ የሀይማኖት አባቶችና ተቋማት ተከታዮቻቸውን ሰላምን በማስተማር ትልቅ ሀላፊነት እንዳለባቸውም አክለዋል።

በመሆኑም የሀይማኖት ተቋማት እርስ በእርስ ተቀራርበው በመወያየት ከፋፋይ አስተሳሰቦችን በመታገል ማህበራዊ መስተጋብሯ የፀና ኢትዮጵያን ለመገንባት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሀፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው ጉባኤው በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን አበርክቶው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይ በአብሮነት በማሰባሰብ አለመግባባቶችን በዕርቅ ለመፍታት የሚያስችል ግብዓት የሚገኝበትና አቅም የሚፈጠርበት ነው ብለዋል።

ሰው በሰውነቱ ብቻ የሚከበርባት አገርን ለመገንባት ሁሉም የበኩሉን ሀለፊነት ሊወጣ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ፀሀፊው በተለይ የዕምነት አባቶች ከምን ግዜውም በላይ ሰላምን መስበክ ይጠበቅባቸዋል።

በየዕምነቱ አስተምህሮት መሰረት ለፈጣሪ ትዕዛዝ በማደር በሰብዓዊነትና ሰውነት ተዋደን የአገርን ሰላም መጠበቅ የጋራ ሀላፊነት ነው።

በተለይ ጦርነት ለአገር አይበጅም ያሉት ጠቅላይ ፀሀፊው ወንድም በወንድሙ ላይ እጅ እንዳያነሳ ማስተማር እና የወንድማማችነትና አብሮነት እሴት ይበልጥ እንዲጎለብት ማድረግ እንደሚገባ አክለዋል።

በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ሀላፊነቱን በተገቢው በመወጣት ለሰላም ግንባታ የበኩሉን ሀላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር፣የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሀፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የፌዴራልና ክልል የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች፣የክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊዎች እና የማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

hiHarari