የልማት ፕሮጀክቶች የጥራት ደረጃ የክልሉን ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ መልኩ ሊከናወን ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ
ሀረር፣መስከረም 16/2017(ሀክመኮ):-የልማት ፕሮጀክቶች የጥራት ደረጃ የክልሉን ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ መልኩ ሊከናወን እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች የጥራት ደረጃ ላይ በተደረገ የመስክ ምልከታ በቀረበ ሪፖርት ላይ የፕሮጀክት ባለቤት ተቋማት በተገኙበት መክሯል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት በክልሉ የልማት ፕሮጀክቶችን በጥራት እና ፍጥነት በማከናወን አበረታች ውጤቶች ማስመዝገብ ተችሏል።
ሆኖም በአንዳንድ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ የጥራት ደረጃን በማስጠበቅ ረገድ ውስንነቶች በመኖራቸው ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የጥራት ጉድለት፤የግብዓት አጠቃቀም፣የክትትል እና የተቋራጮች ብቃት ማነስ ለዘርፉ ፈተናዎች በመሆናቸው የዘርፉን ክፍተቶች ማረም እንደሚገባ አክለዋል።
በክልሉ ተግባራዊ የሚደረጉ የልማት ፕሮጀክቶች የጥራት ደረጃ የክልሉን ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ መልኩ ሊተገበሩ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
በመሆኑም የጥራት ደረጃ ውስንነት የተስተዋለባቸው የልማት ፕሮጀክቶች በሚፈለገው የጥራት ደረጃ እና ፍጥነት እንዲከናወኑ ለማስቻል ባለቤት ተቋማት ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በልማት ፕሮጀክቶች ላይ ለሚከሰተው የጥራት ጉድለትና መጓተት ተጠያቂ መደረግ ያለባቸው አካላት በህግ-እንዲጠየቁ እንደሚደረግም ገልፀዋል።


0 Comments