Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለስኬት መብቃት ለጀመርነው የብልፅግና ጉዞ አንዱ ማሳያ ነው -ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለስኬት መብቃት ለጀመርነው የብልፅግና ጉዞ አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር ገለፁ።

በሀረሪ ክልል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለስኬት መብቃቱን ተከትሎ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሄደ።

ሰልፈኞቹ በድጋፍ ሰልፉ ላይ በህብረት ችለናል፣የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ምልክት ነው፣ግድባችን በራስ አቅም በአፍሪካዊነት ኩራት የተገነባ እውነት ነው የሚሉ እና ሌሎች መፈክሮችን አሰምተዋል።

የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ሰብሳቢ ወይዘሮ ሮዛ ኡመር በድጋፍ ሰልፉ ላይ ባስተላለፉት መልዕከት ታላቁ የህዳሴ ግድብ የመደመር ትውልድ አሻራ የወል እውነት ማሳያ ሌላ የምስራችና ተጨማሪ ድል ነው ብለዋል።

ብልጽግና አካታችነትና ፍትሃዊነትን መርህ አድርጎ ለሁንተናዊ ተምሳሌትነት እየተጋ ሀገራዊ ልዕልናን እያበሰረ ጉዞውን ቀጥሏል።

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለስኬት መብቃትም ለዚህ አንዱ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ገልፀዋል።

ጥንት አባቶቻችን የአፍሪካውያን የድል ምልክት የሆነውን አድዋን በደማቸው እንዳስመዘገቡት ሁሉ የመደመር ትውልድ በላቡ ያነፀው የአርበኝነት ማሳያ የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብም ከእራስ አልፎ ለወንድም አፍሪካዊያንም ኩራት የሆነ ነው።

ብሔራዊ ክብርን ያሰጠበቀ፣የትውልድ ቅብብሎሽና የትጋት ውጤት የሆነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ ተጨማሪ ብስራትን በማስቀጠል የልዕልናችንን መንገድ ያመላከተ ነው።

ግድቡ ብዝሃነታቻችንን ያደመቀ አንድነታችንን ያፀና በወል ሀገር የወል እውነትን ያዳበረ ታላቅ የስኬት አሻራና ድል መሆኑን አመላክተዋል።

በለውጡ መንግስት ቆራጥ አመራርና በነቃ የህዝብ ተሳትፎ ለስኬት የበቃው የህዳሴ ግድብ በመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት በላብ እና ደም የተገኘ
ከዓድዋ ቀጥሎ የተመዘገበ የጥቁር ህዝቦች ደማቅ የድል ታሪክ ነው።

የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ውስጣዊና እና ከውጭ የነበሩ ጫናና ውስብስብ ተግዳሮቶችን አልፎ
ያለምንም የውጭ ብድርና እርዳታ በውስጥ አቅም የተገነባና ሲሆን እኛ ኢትዮጵያውያን ስንተባበር ማንኛውንም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ጀምረን ማጠናቀቅ እንደምንችል የመፈፀም አቅማችን በተጨባጭ የታየበት ነው።

ግድቡ ለኢትዮጵያዊያን የዘመናት ቁጭት ምላሽ የሰጠና የመንፈስ ጥንካሬ የታየበት ታላቅ ገድል ነው።

በህብረት እውን ያደረግነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ የሉአላዊነታችን ግርማ ሞገስ የብሄራዊ ኩራታችን ምንጭ የአንድነታችን ካባ ምልክት ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እኛ ኢትዮጵያውያን ከተመጽዋችነት መላቀቅ እንደምንችል ያመላከተ የአመራር ብቃትና የህዝብ አንድነት የታየበት ጭምር ነው።

የክልላችን ህዝብም ለግድቡ በስኬት መጠናቀቅ ቦንድ በመግዛት ላደረገው ተሳትፎ ብሎም ሀብት የማሰባሰብ ስራውን በሀላፊነት ወስደው በማስተባበር የላቀ ተሳትፎ ላደረጉ አካላት እና ለግድቡ ስኬት በሳልና ቆራጥ አመራር በመስጠት ይህ ውጤት እንዲመዘገብ ከፍተኛ አስተዋፆ ላበረከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ምስጋና አቅርበዋል።

በመርሀ-ግብሩ ላይ በብልፅግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ፣የሀረሪ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም ፣የሀረሪ ብሄራዊ ጉባኤ አፈ-ጉባኤ አቶ ሙህየዲን አህመድ፣የሀረሪ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ማሂር አብዱሰመድ፣ የክልሉ አመራሮች እንዲሁም የከተማና ገጠር ወረዳ ነዋሪዎች እና የክልሉና የፌዴራል የፀጥታ ተቋማት ተገኝተዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

hiHarari