በሐረሪ ክልል በሚገኙ የወጣቶች ስብዕና ልማት ማዕከላት በክረምት ወራት ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የክልሉ ወጣቶች ስብዕና ልማት ማዕከል አስታወቀ።
-የሀረሪ ክልል ወጣቶች ስብዕና ልማት ማዕከል ስራ አስኪያጅ ወጣት ኢምራን አብዱሰመድ ማዕከሉ በክረምት ወራት ያከናወናቸውን አበይት ተግባራት በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል።
የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራቸው ከሚገኙ ስራዎች መካከል ወጣቶትን በስብዕና ማዕከላት ተጠቃሚ ማድረግ አንዱ መሆኑንም የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ ገልጿል፡፡
በክልሉ በሚገኙ የወጣት ስብዕና መገንቢያ ማዕከላት በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት 16 ዓይነት አገልግሎቶችን ለወጣቶች እንዲሰጡ መደረጉንም አክሏል።
ማዕከላቱ ወጣቶቹ ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ከማስቻሉም በላይ ጊዜያቸውን በአለባሌ ቦታ እንዳያባክኑ ከፍተኛ ሚና አበርክቷል፡፡
በተለይ ማዕከላቱ እየሰጡት በሚገኘው አገልግሎት ወጣቱን በሥነ-ምግባር ከማነፅ ባሻገር ተሰጥኦቸውን አውጥተው እንዲያዳብሩ ምቹ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ጠቁሟል።
ማዕከሉ ወጣቶች ዕውቀት የሚገበዩበትን ስርዓት በመፍጠር ወጣቱ የእረፍት ግዜውን በአለባሌ ቦታ እንዳያባክን ለማስቻል ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ነው።
የሳይንስ ክበብ፣የስዕል ችሎታ ማዳበሪያ፣ የሕይወት ክህሎት ስልጠና፣ የኪነ ጥበብ ትምህርቶች እና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ማዕከሉ እየሰጣቸው ከሚገኙ አገልግሎቶች ውስጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን ስራ አስኪያጁ ጠቅሰዋል።
ወጣቶች በማዕከላቱ የኮምፕዩተር፣የጂም አገልግሎት፣ውዝዋዜ እና የተለያዩ የኪነ ጥበብ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ ተደርጓል።
በማዕከሉ በኪነጥበብ፣ በስነ-ተዋልዶ፣በፈጠራ እና ሰርቶ ማሳያ፣ በኢንፎርሜሽን ኮሙንኬሽንና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ለስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ትኩረት በመስጠት ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ነው የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ ወጣት ኢምራን አብዱሰመድ የገለፀው።
በያዝነው አመትም የወጣቱን ማሕበራዊ፣ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሁሉን አቀፍ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
በማዕከሉ እየተሰጡ ከሚገኙ አገልግሎቶች መካከል በተለይ የኮምፕዩተር አጠቃቀም ስልጠናዎች የዲጂታል ክህሎታቸውን በማዳበር ወቅቱ ለሚጠይቀው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዝግጁ እያደረጋቸው እንደሚገኝም የማዕከሉ ተጠቃሚ ወጣቶች ገልፀዋል።
0 Comments