በሀረር ከተማ ትውልድን የሚሻገር ተጨባጭ ለውጥ ተመልክተናል -የሀረሪ ተወላጆች
በሀረር ከተማ እና በከተማው በሚገኘው የአለም አቀፉ የጁገል ቅርስ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች ከዛሬ ባለፈ ለነገው ትውልድ መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን ተመልክተናል ሲሉ የሀረሪ ተወላጆች ገለፁ።
የሀረሪ ብሄራዊ ጉባኤ በነገው ዕለት በሚካሄደው 6ኛ ዙር 4ኛ አመት 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ለመሳተፍ ወደ ክልሉ የገቡ የሀረሪ ተወላጆች በክልሉ የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ተመልክተዋል።
በአለም አቀፉ የጁገል ኮሪደር መልሶ ልማት፣በከተማው የተከናወኑ የኮሪደር ልማቶች እና የህዝብ መናፈሻዎች ላይ ነው የመስክ ምልከታውን ያደረጉት።
በመስክ ምልከታው ላይ እንደገለፁት በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች የሀረርን የገናናነት ዘመን የሚመልሱና ከዛሬ ባለፈ ለነገው ትውልድ መሰረት የሚጥሉ ናቸው።
የኮሪደር ልማቱ በከተማው ይስተዋል የነበረውን የፅዳት ጉድለት በማስቀረት ንፁህ፣ ውብና ምቹ የመኖሪያ አካባቢ እንዲሆን አስችሏል ብለዋል።
በተለይ ጥንት አባቶች አንፀው ያቆዩትን አለም አቀፉን የጁገል ቅርስ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ የተሰራው የመልሶ ማልማት ስራም ቅርሱ ቀደም ሲል ከተደቀነበት አደጋ ከመታደግ ባለፈ አካባቢው ለጎብኚዎችና ለነዋሪዎች ምቹ ሆኖ በመመልከታቸው የፈጠረባቸው ደስታ ገልፀዋል።
ይህም ትውልዱ ከታሪቅ ተወቃሽነት ወደ ታሪክ ሰሪነት ያሸጋገረ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም አመራሩ ከንግግር ባለፈ ህዝብና ተቋማትን በማስተባበር ያለምንም ተጨማሪ ወጪ ያከናወነው በተግባር የተገለፀ ውጤት ሁሌም ሲዘከር የሚኖር ነው ብለዋል።
ካሁን ቀደም ባልተለመደ መልኩ በከተማው የተገነቡ የኮሪደር ልማት ስራዎች ውብ፣ ምቹና ዘመናዊነትን ያላበሱ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህም የሀረርን ቀደምት ገናናነት የሚመልሱና መሆናቸው አንስተዋል።
የክልሉ መንግስት በሚያከናውናቸው ስራዎች ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።
0 Comments