በሀረሪ ክልል ወንጀልን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል-የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን
በክልሉ ባለፍት ስድስት ወራት ፖሊስ ማህበረሰቡን በማሳተፍ ወንጀልን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን የሀረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ገናናው ጥበቡ ገለጹ።
ምክትል ኮሚሽነሩ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ባለፍት ስድስት ወራት በክልሉ ማህበረሰቡን በማሳተፍ በተከናወኑ ስራዎች የክልሉን አንፃራዊ ሰላም ማስቀጠል መቻሉን ገልጸዋል።
በዚህም የክልሉ ማሕበረሰብ ወንጀልን በመከላከል ሥራ ከጸጥታው መዋቅር ጋር በባለቤትነት እንዲሳተፍ በመደረጉ ወንጀል እንዲቀንስ ተደርጓል ብለዋል።
በከተማው ወንጀል ይፈጸምባቸዋል ተብሎ በተለዩ አካባቢዎች ላይ ማሕበረሰቡ በራሱ ባደረገው ትብብር ውጤታማ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
ከዚህ ባሻገርም የማሕበረሰቡን የወንጀል መከላከል ግንዛቤን የማሳደግ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።
የጸጥታ ሥራውን ዘመናዊ ከማድረግ አንጻር በከተማው የደህንነት (cctv) ካሜራዎች የመትከል ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
ካሜራዎቹ በክልሉ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በመከታተል ወንጀል ከመከሰቱ በፊት ቀድሞ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ብሎም ለወንጀል መከላከል ሥራው ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቅሰዋል፡፡
ኮሚሽኑ ባለፍት ስድስት ወራት በክልሉ በትራፊክ አደጋ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስ አዳዲስ የትራፊክ ፖሊሶችን በማሰልጠን ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ኃይማኖታዊና ህዝባዊ የአደባባይ በዓላትን በሰላማዊ መንገድ ማካሄድ የተቻለበት ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ አንስተዋል።
በወንጀል መከላከል ረገድ በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት በስርቆትና ተያያዥ ከቀላል እስከ ከባድ የወንጀል ድርጊት የፈጸሙ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉን አስረድተዋል።
ጥናትን መሰረት በማድረግ በተሰሩ ስኬታማ የኦፕሬሽን ስራዎች መሰራቱን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተው የዲሲፕሊን ጥሰት የፈጸሙ የፖሊስ አመራሮችና አባላት ላይ ከቀላል እስከ ከባድ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ፖሊስ የወንጀል መከላከሉን ስራ ህዝቡን በጎኑ በማሰለፍ የአንበሣው ድርሻ እንዲጫወት የሰላም ባለቤት በማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጥብቅ ዲስፕሊን እየሰራን የክልላችንን ሰላም እናስከብራለን ብለዋል።
0 Comments