ሀገራችን አዲስ የመንሰራራት ዘመን ጅምሮ ላይ ትገኛለች-ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ
ሀገራችን አዲስ የመንሰራራት ዘመን ጅምሮ ላይ ትገኛለች ሲሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ሚዲያ ገፃቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት የኢትዮጵያ ታሪክ በብዙ ውጣ ውረዶች፣ ትግሎች እና ጀግንነቶች የተሞላ ነው።
በየዘመናቱ የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበርና ነፃነትን ለማስረገጥ አባቶቻችን እና እናቶቻችን የከፈሉት መስዋዕትነት ደማቅ ነው።
አሁን ደግሞ ሀገራችን አዲስ የመንሰራራት ዘመን ጅምሬ ላይ ትገኛለች የዚህ ዘመን ምልክት ደግሞ የሕዳሴው ግድብ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ይህ ግድብ የብረት እና ኮንክሪት ስብስብ ብቻ አይደለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የኢትዮጵያን የመነሳትና ራስን የመቻል መንፈስ ህያው ምስክር
የኢትዮጵያ ማንሠራራት ጅማሮ የብዙ ትናንሽ ጠብታዎች ድምር ውጤት መገለጫ ነው ብለዋል።
የህዳሴ ግድባችን በ’ደም ጠብታ!’ የሚገለጽና የሀገራችን ህልውና እና የሉአላዊነት ዋጋን የሚያመላክት ነው።
የጠላት ጥቃት በተደቀነ ጊዜ የሀገር ክብርን ለማስጠበቅ የወደቁ ጀግኖች ለሀገራቸው የከፈሉትን ደምና የመጨረሻ ዋጋ ይመሰክራል።
ይህ ደም ለሀገራችን ህይወት የሰጠና ለውጭ ጠላቶች ሳይበገር ኢትዮጵያዊነትን አጽንቶ የኖረ ነው።
በተመሳሳይም የህዳሴ ግድብ ግንባታ ብዙ ውጣ ውረዶች እና ብርቱ ትግሎችን በጽናት መሻገር የጠየቀ ነው።
የተለያዩ ሴራዎችን እና ችግሮችን በጽናት በመቋቋም የተገኘ የላቀ እና የደመቀ ታሪካዊ ስኬት ነው መሆኑን ገልፀዋል።
ዛሬ ግድባችን የተሻገርነው የደም መስዋዕትነት እና የትግል ምልክት ሆኖ በታላቅ ድምቀት ለምረቃ ሊበቃ ከፊታችን ቆሟል።
የህዳሴ ግድባችን ‘የላብ ጠብታ!’ ነው።
ይህ የኢትዮጵያውያን የድካም ፍሬ፣ የጥረታቸው እና የቁርጠኝነታቸው ምስክር ነው።
ግድቡን የዛሬው ቁመናው ላይ ለማድረስ ያወጡት ገንዘብ፣ የገበሩት እውቀት እና ያፈሰሱት ላብ ጭምር መገለጫ ነው።
በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቀን ከሌሊት በትጋት ያንጠባጠቡትን ላብ የሚያሳይ ድንቅ አሻራ ነው።
ህዳሴ ግድባችን የኢትዮጵያውያን የሀዘን፣ የተስፋ እና የትግል ዕንባ ነው።
ይህ የብዙ ዘመናት የድህነት፣ የሀዘን የቁጭት እና የብስጭት ዕንባ ዛሬ የህዳሴ ግድብን እውን አድርጓል።
ይህ ግድብ ለትውልድ የሚታይ ተስፋን እና ደስታን የሚያበስር፣ የዕንባ ጠብታን ወደ ደስታ ዕንባ የቀየረ ነው።
ህዳሴ ግድብን የኢትዮጵያ ማንሠራራት ጅማሮ ከሚያደርጉት ቁልፍ ነጥቦች አንዱ ነው።
የህዳሴ ግድብ ‘የውሃ ጠብታ’ ነው።
በእርግጥም የውኃ ጠብታ የህይወት እና የብልጽግና ምንጭ ነው።
ይህ ግድብ የሀገራችን እድገት፣ ለትውልድ ህይወት እና ብልጽግና ምንጭ መሆኑን ያሳያል። ይህ ግድብ የሀገራችን የኢኮኖሚ ህይወትና የእድገት ምንጭ እንደሆነ ያረጋግጣል።
የዚህ ዘመን ትውልድ እና አመራር በራስ መተማመን እና ቁርጠኝነት የአገራችን ማንሰራራት ጅማሬን ያበስራል።
በአጠቃላይ ይህ ግድብ በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት፣ መስዋዕትነት እና እምነት የተገኘ ነው።
ጠቅላይ ሚንስትራችን እንደጠቀሱት “የደም ጠብታ፣ የላብ ጠብታ፣ የዕንባ ጠብታ፣ የውኃ ጠብታ” ድምር ውጤት ነው።
ይህ ግድብ ህያው ምልክት ሆኖ ‘ለትውልድ ሲመሰክር የሚኖር ቋሚ ምስክርና የኢትዮጵያ ማንሰራራት ጅማሮ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።

0 Comments