የንግዱ ማህበረሰብ ለክልሉ ልማት እያበረክተ የሚገኘውን አስተዋፆ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ
ሐረር፣ግንቦት 27/2017(ሐክመኮ):-የንግዱ ማህበረሰብ ለክልሉ ልማት እያበረከተ የሚገኘውን አስተዋፆ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
በሐረሪ ክልል “የንግዱ ማህበረሰብ ሚና ለሁንተናዊ ብልፅግና”በሚል መሪ ቃል ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ሲደረግ የነበረው ውይይት ተጠናቋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ፅሁፍ በክልሉ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ እስማኤል ዩሱፍ ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በውይይት መድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት
በአገሪቱ እየተመዘገበ በሚገኘው ልማት የንግዱ ማህበረሰብ አበርክቶ የጎላ ነው ብለዋል።
በተለይ የአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከንግዱ ማህበረሰብ ዕድገት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው
በመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ እራሱ ን እና ንግዱን በማሻሻል ለአገሪቱ ዕድገት የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል።
ከለውጡ ወዲህ መንግስት ለንግዱ ዘርፍ በሰጠው ትኩረት በርካታ ማሻሻያዎችን በማድረግ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በክልሉ ከጥቂት ቀናት በፊት ብቻ 2.9 ቢሊየን ኢንቨስትመንት ላስመዘገቡ 28 አልሚዎች 56 ሺ ካሬ ሜትር መሬት ተላልፎ ተሰጥቷል።
በቀጣይም የአገልግቶት አሰጣጥ ችግሮች ና ብልሹ አሰራሮችን ለማረም አስፈላጊውን እርምጃ ከመውሰድ ጀምሮ ለአልሚዎች አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል።
ሆኖም መሬት የወሰዱ አልሚዎች የወሰዱትን መሬት በአጭር ግዜ ወደ ስራ በማስገባት ለታለመለት አላማ ሊያውሉ እንደሚገባ ገልፀዋል።
የክልሉ መንግስት ህገ ወጥ የኮትሮባንድ ንግድ ቁጥጥር ስራ ከምን ግዜውም በላይ አጠናክሮ እንደሚቀጥልምገልፀዋል።
በመሆኑም የንግዱ ማህበረሰብ ህግና ደንቡን ተክትሎ በመነገድ ከንግድ አሻጥር እራሱን ሊያርቅ እንደሚገባና የስራ ዕድል በመፍጠር ወጣቱን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በበኩላቸው የክልሉ መንግስት አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ያከናወናቸውን ተግባራት በማድነቅ የክልሉን ልማት እንደሚደግፉ ገልፀዋል።


0 Comments