በክልሉ ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ጥረት ይጠናከራል-ኮሚሽነር አዳል ሙላቱ
በሀረሪ ክልል ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
የክልሉ ሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አዳል ሙላቱ እንዳሉት፥ ሙስናን መከላከል የሕዝብና የመንግሥት ሀብትን ለታለመለት ዓላማ ብቻ በማዋል የጋራ ዕድገትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው።
በመሆኑም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ኅብረተሰቡ ጋር እየተደረገ ያለው ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን የመታገል ተግባር መሻሻሎች እያሳየ መምጣቱን ገልጸው፥ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።
ሙስና ለሀገርና ህዝብ ጠንቅ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ፥ ለዚህም ሙስናን የሚጸየፍና የሚታገል ህብረተሰብን መፍጠር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የመንግስትና የህዝብን ሀብት ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል ለማድረግ በየሴክተሩ ያሉ የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል ኦፊሰሮች የመከታተልና የመቆጣጠር ስራ በትኩረት መሰራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ሙስና ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ፀረ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ በያዝነው የበጀት ዓመትም የተሻለ የሙስና መከላከል ሥራ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱን አመልክተዋል።
በሁሉም መስክ ሙስናና ብልሹ አሠራርን በማረም የመንግሥት አገልግሎት በዜጎች ተዓማኒነት እንዲኖረው ሁሉም ባለድርሻ አካል በቁርጠኝነት እንዲታገል ኮሚሽነር አዳል ጠይቀዋል።
በተለይም የሚዲያ አካላት የፀረ-ሙስና ትግሉና ትውልድን በስነ-ምግባር የማነጽ ተግባር የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባብ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በያዝነው የበጀት ዓመትም ኮሚሽኑ ሙስናን ለመከላከል የተለያዩ ስልጠናዎችን እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄዎችን እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
0 Comments