በክልሉ ለ12 ሺ ዜጎች የ 5 ሚሊየን ኮደርስ ስልጠና ተሰጥቷል-ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ
በሀረሪ ክልል ለ 12 ሺ ዜጎች የ 5 ሚሊየን ኮደርስ ስልጠና መሰጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
በክልሉ የዜጎችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎት በማዳበር እንደ ሀገር የተጀመረውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ለማሳለጥ ለ 5 ሚሊዮን ኮደርስ ስልጠና ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳድሩ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ገልፀዋል።
በዚህም በክልሉ 12 ሺ ዜጎች በፕሮግራሚንግ፣ዳታ ሳይንስ፣አንድሮይድና ተያያዥነት ያላቸው ስልጠናዎችን እንዲወስዱ መደረጉን አክለዋል።
ስልጠናውን ላጠናቀቁ 7 ሺ ሰልጣኞች በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የምስክር ወረቀት መሰጠቱንም ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በክልሉ ከ 200 ሺ በላይ ነዋሪዎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።
የፋይዳ መታወቂያ ታማኝነትን በማስፈን፣ የተቋማትን ሥራን በማቀናጀት የሀገር እና የዜጎችን ደኅንነት በማስጠበቅ ረገድ ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች በብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ መስጫ ማዕከላት በመገኘት እንዲመዘገቡም ጥሪ አቅርበዋል።
0 Comments