Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

ስኬቶቻችን የሰንደቃችንን ከፍታ የሚጨምሩ ናቸው

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት እመርታዊ ስኬቶችን እያስመዘገበች የሚመጥናትን ከፍታ እየያዘች ትገኛለች ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ የሚከበረውን የሰንደቅ ዓላማ ቀን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ስኬቶቻችን የሰንደቃችንን ከፍታ የሚጨምሩ ናቸው ብሏል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ስኬቶቻችን የሰንደቃችንን ከፍታ የሚጨምሩ ናቸው

ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት እመርታዊ ስኬቶችን እያስመዘገበች የሚመጥናትን ከፍታ እየያዘች ትገኛለች፡፡

ለዘመናት የቁጭት እና እንጉርጉሮ ትርክት ምንጭ የነበረውን ዓባይን ገርታ የኃይል እና ብርሃን ምንጭ አድርጋለች፡፡

በንጋት ኃይቅ በምግብ ሉዓላዊነቷ ላይ ጉልህ ሚና የሚጫወት የዓሣ ምርት ማግኘት ችላለች፤ ዐዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ደሴቶችንና ከተሞችን ፈጥራለች፡፡

የዓባይን የቁጭት ትርክት ወደ ድል እና አሸናፊነት ብስራት ቀይራለች፡፡

ተጨማሪ የኃይል ምንጮችን ከውኃ እስከ እንፋሎት፣ ከፀሐይ ብርሃን እስከ ኑውክሊየር ኃይል እና ነፋስ በመገንባት ላይ ናት፡፡

እነዚህ ሁሉ የሰንደቋን ከፍታ እና ተምሳሌትነት የሚያጎሉ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ከገጸ ምድር ባሻገር በከርሰ ምድር ያሉ ሀብቶቿን ወደ መጠቀም ተሸጋግራለች፡፡

በተፈጥሮ ጋዝ ማውጣት የታየውን ስኬት ለማላቅ፣ በነዳጅ ዘይትም ለመድገም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ጀምራለች፡፡

የግብርና ዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ የዐፈር ማዳበሪያ በራሷ ለማምረት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሳለች፡፡

የሕዝቧን የአኗኗር ዘይቤ ለመቀየር ከቢሮ እስከ ግቢ በሚል ጀምራ፣ ከከተማ እስከ ገጠር ወደሚል ተሸጋግራለች፡፡

በአዲስ አበባ የተጀመረው የከተሞችን ገጽታ የመቀየር ንቅናቄ ዘመናዊነትን፣ የስማርት ሲቲ ጽንሰ ሐሳብን እና ሰውን ከተፈጥሮ የማስማማት ልምምድን ያስተዋወቀ ነው፡፡

ይህም የዲፕሎማሲ ማእከል የሆነችውን መዲናችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ገጽታ የሚያጎላ፣ የሰንደቃችንን ከፍታ
የሚጨምር ሆኗል፡፡

ከተሞቻችንን የማዘመኑን ጅማሮ ወንዞቻችን በማከም የተፋሰሶችን ደኅንነት የሚያረጋግጥ ሆኗል፡፡

ከእንጦጦ ጀምሮ እየተሠራ ያለው የወንዞች ዳርቻ ልማት የአዋሽ ተፋሰስን ሥነ ምኅዳር ጭምር የሚያክም ለአካባቢ ጥበቃ አብነት ነው፡፡

የገጠር አኗኗር ዘይቤያችንን በማዘመን ኢትዮጵያን በበጎ የምትመሰል ሀገር የማድረግ ጥረታችንም ፍሬው እየታየ ነው፡፡

እነዚህ ሁሉ የሰንደቃችንን በኩራት መውለብለብ የሚያጎሉ የትጋታችን ውጤቶች ናቸው፡፡

ዛሬ የምናከብረው የሰንደቅ ዓላማ ቀን በነፃነት ቀን የተገኘ አይደለም፤ ነፃ ሆኖ ለሌሎች ነፃነት ከፍ ብሎ ሲውለበለብ የታየ የነፃነት ምልክት እንጅ፡፡

ነፃነቱን ለማስከበር ግን ቀደምቶቻችን ደም፣ ሥጋ እና ዐጥንት ገብረዋል፡፡

ኢትዮጵያን የዓለም የነፃነት ቀንዲል አድርገው አስረክበውናል፡፡ ዛሬም እንደትናንቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በደም እና በዐጥንት ለማስበር የቆረጡ ጀግኖች አሉን፡፡

በምድር፣ በአየር፣ በባሕር እና በሳይበር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስከበር ሰንደቋ የነፃነት ተምሳሌትነቱ እንዲቀጥል የሚተጉ
ጀግኖቻችን አሉ፡፡

የሰንደቅ ዓላማ ቀንን የምናከብረው በሁሉም ግንባር፣ በሁሉም ዓውድ ስለኢትዮጵያ ዋጋ የሚከፍሉ ጀግኖቻችን በማመስገን፣ ሰንደቃችንንም በክብር ከፍ አድርገን በማውለብለብ፣ ለላቀ ከፍታው እንደምንተጋ ቃል በመግባት ነው፡፡

የተጀመሩ ትልልቅ የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ደግሞ ያለስስት በጋራ መጣር፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ ማናቸውንም ዋጋ መክፈል ከዜጎች ይጠበቃል፡፡

እንኳን ለሰንደቅ ዓላማ ቀን አደረሳችሁ!

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ጥቅምት 3/2018 ዓ/ም

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish