ፓርቲው ነጣጣይ ትርክቶችን በማሸነፍ አሰባሳቢ ትርክቶች የበላይነት እንዲይዙ ያሳለፈው ውሳኔ የሀገረ መንግሥት ግንባታው እንዲሳካ አበርክቶው የጎላ ነው -የሀረር ከተማ ወጣቶች
ሐረር፤የካቲት 1/2017(ሀክመኮ):-የብልፅግና ፓርቲ ነጣጣይ ትርክቶችን በማሸነፍ አሰባሳቢ ትርክቶች የበላይነት እንዲይዙ በጉባኤው ያሳለፈው ውሳኔ የሀገረ መንግሥት ግንባታው እንዲሳካ አበርክቶው የጎላ መሆኑን የሀረር ከተማ ወጣቶች ገለፁ።
የብልፅግና ፓርቲ ወደ ስልጣን ከመጣ ማግስት ጀምሮ ቀድሞ የነበሩ ነጣጣይ ትርክቶችን በማስቀረት፤አሰባሳቢ ትርክቶች የበላይነት እንዲይዙ በማስቻል፤ህብረ ብሄራዊ አንድነት እንዲጎለብት ማስቻሉን የሀረር ከተማ ወጣቶች ገልፀዋል።
ይህም ቀድሞ የነበረውን እርስ በእርስ የመገፋፋት እና የጥላቻ ፖለቲካን በማስቀረት ቀድሞ ሀረር ትታወቅበት የነበረውን የአብሮነት፤የሰላም እና ፍቅር እሴቶች ይበልጥ እንዲጎለብቱ ማስቻሉን አስገንዝበዋል።
በክልሉ የተፈጠረው ህብረ-ብሄራዊ አንድነት ማህበረሰቡ በተባበረ ክንድ መንግስት የማያከናውናቸውን የልማት ስራዎች በመደገፍ ለልማት ስራዎች ምቹ ሁኔታን መፍጠሩንም ገልፀዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ባካሄደው ሁለተኛ ጉባኤው የብሔራዊነት ገዥ ትርክትን በመፍጠር የሕዝቦች ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ይበልጥ እንዲጠናከር የተጀመሩ ሥራዎችን ለማጎልበት ያሳለፈው ውሳኔ በክልሉ ህብረ ብሄራዊነት ይበልጥ እንዲሰርፅ የሚረዳ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በማኅበረሰቡ መካከል መግባባትን የሚፈጥሩ ሕዝባዊ ውይይቶችን ለማካሄድ የተቀመጠው አቅጣጫም ማህበራዊ ግንኙነቶችን ይበልጥ የሚያጠክር ነው።
ነጣጣይ ትርክቶችን በማሸነፍ አሰባሳቢ ትርክቶች ይበልጥ እንዲጎለብቱ በማድረግም የሀገረ መንግሥት ግንባታው እንዲሳካ አበርክቶው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይ በመደመር እሳቤ አካታች የፖለቲካ ባህል እንዲገነባ እና በሀገር ጉዳይ ሁሉም እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ይበልጥ በአገራቸው ጉዳይ በባለቤትነት መንፈስ እንዲረባረቡ ያስችላል ብለዋል።
በመሆኑም ፓርቲው ገዥ ትርክቶችን በመፍጠር ሁሉም ኢትዮጵያውያንን ለጋራ ግብ ለማነሳሳት ላሳለፈው ውሳኔ እውን መሆን ወጣቶቹ በአንድነት እንደሚሰለፉ አረጋግጠዋል።
በተለይ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች የሚሰራጩ ነጣጣይ የጥላቻ መልዕክቶችን በማጋለጥ ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ እና የወንድማማችነት እሴት ይበልጥ እንዲጎለብት የበኩላቸውን ሀላፊነት እንደሚወጡ ወጣቶቹ ገልፀዋል ።


0 Comments