የክልሉ ኅብረተሰብ ለሕዳሴ ግድቡ እያደርገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ
ሐረር፤ግንቦት 5/2017 (ሐክመኮ):-የክልሉ ህዝብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የሐረሪ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽ/ቤት እና የክልሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ ጠየቁ።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ የሐረሪ ክልል ህዝብ ያልተቋረጠ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የገለፁት የክልል የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ ማህበረሰቡ አጋርነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለሀገር ሁለንተናዊ ልማት እና ዕድገት የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ ነው ያሉት ሀላፊው በክልሉ የተጀመረውን ንቅናቄ ከማጠናከር ባሻገር፣ በቦንድ ሽያጭ እና በ 8100 አጭር የጽሑፍ መልዕክት ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅትም በክልሉ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በሦስት ወራት ግዜ ውስጥ 3 ሚሊየን ብር ከቦንድ ሽያጭ ለመሰብሰብ በዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከገቢ አሰባሰብ ስራ በተጨማሪ በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም አክለዋል፡፡
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከዳር ለማድረስ ሁሉም ማህበረሰብ በጋራና በአንድነት በመሆን ቀድሞ ሲያደርገው የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም አገሪቱ ያላትን ሀብት እና እውቀት በመቀመር የአንድነታችን ምልክት ለሆነው ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እናውላለን ብለዋል።
0 Comments