የክልሉ መንግስት በገባው ቃል መሰረት ምትክ የቤት መስሪያ መሬት ተረክበናል-የልማት ተነሺዎች
ሐረር፤ሚያዚያ 19/2017(ሐክመኮ):-በሐረር ከተማ መንግስት ለልማት ተነሺዎች ምትክ የቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት በገባው ቃል መሰረት የተዘጋጀላቸውን የቤት መስሪያ መሬት መረከባቸውን የአሚር ኑር ወረዳ የልማት ተነሺዎች ገለፁ።
በሐረር ከተማ አሚር ኑር ወረዳ በተለምዶ ገንደ ፌሮ በመባል በሚጠራው አካባቢ ለሚከናወነው የኮሪደር ልማት ከአካባቢው በልማት የተነሱ ነዋሪዎች በተገባላቸው ቃል መሰረት ምትክ የቤት መስሪያ ቦታ መረከባቸውን ገልፀዋል።
በተለይ የከተማ የመሬት ደረጃን የጠበቀ ቦታ በፍጥነት በመረከባቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸውም ነው የገለፁት።
የኮሪደር ልማቱ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች እና ለመኖሪያ ምቹ የሆነች ከተማን ለማስረከብ የሚያስችል ነው ያሉት የልማት ተነሺዎቹ መንግስት የጀመረውን የኮሪደር ልማት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር መዓረግ የሐረሪ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ በበኩላቸው ለ 25 የልማት ተነሺዎች የከተማውን የመሬት ደረጃ የጠበቀ ቤት የመስሪያ ቦታን ጨምሮ የካሳ ክፍያ መፈፀሙን ገልፀዋል።
በመሬት ዝግጅቱ በተለይ የልማት ተነሺዎችን ማህበራዊ መስተጋብር አስጠብቆ ለማስቀጠል ትኩረት መሰጠቱንም አክለዋል።
በቀጣይም የዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ ለተቀሩ የልማት ተነሺዎች የቤት መስሪያ ቦታ ለመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ ነው አቶ ሙክታር ሳሊህ የገለፁት።
ካሁን ቀደም በከተማው ለኮሪደር ልማት ተነሺዎች ምትክ የመስሪያ ቦታ መሰጠቱ የሚታወስ ነው።


0 Comments