የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከፍተኛ ስኬት አስመዝግቧል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
በብቃት የመራናቸው የሪፎርም ሥራዎች በየዘርፉ አበረታች ውጤቶችን አስገኝተውልናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
በማብራሪያቸውም፤በሪፎርሙ ዋና ዋና ዓላማ ተብለው የተለዩ ዓላማዎችን አብራርተዋል።
በዚህም መሠረት፤የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን ማረቅ፣የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን ማሻሻልና ማዘመን፣ የዘርፎችን ምርታማነትና የመወዳደር ዐቅማቸውን ማሳደግ፣የማስፈጸም ዐቅማችንን ማሳደግ፣ዘላቂ የፋይናንስ ሥርዓትና ጥራትን ማሳደግ የሚሉት ዋና ዋና የሪፎርሙ ዓላማዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።
በሪፎርሙ ከፍተኛ ለውጥ መገኘቱን ጠቅሰው፥ ከእነዚህ መካከልም ገቢ የመሰብሰብ ዐቅም እና የወጪ ንግድ ማደጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ከዕዳ ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያም፤ የእኛ ዕዳ ከ23 ቢሊየን ዶላር አይበልጥም፤ ከዕዳ ጋር በተያያዘ ከሀገራችን ቀድመው ከፍተኛ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራትም እስከ 300 ቢሊዮን የሚደርስ እዳ እንዳለባቸው መታወቅ አለበት ብለዋል።
በንጽጽር ሲታይ የእኛ ሀገር ያለባት ዕዳ ትንሽ ነው፤ ሪፎርሙ ከፍተኛ ለውጥና ስኬት ስላመጣ ኢትዮጵያ አሁን ዕዳ ለመክፈል ምንም ችግር እንደሌለባት ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።
የተሳካ ሪፎርም መምራት በመቻላችን፤ከለውጡ ወዲህ የኢትዮጵያ መጠባበቂያ (ሪዘርቭ) ከ10 እጥፍ በላይ አድጓል ሲሉም ተናግረዋል።
0 Comments