የአንደኛ መንገድ ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ የኮሪደር መልሶ ልማት ስራ ይከናወናል – አቶ ሙክታር ሳሊህ
ሀረር ታህሳስ 20/2017(ሀክመኮ)፦ አለም አቀፉ የጁገል ቅርስ አካል የሆነው የአንደኛ መንገድ ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ የኮሪደር መልሶ ልማት ስራ ለማከናወን እንደሚሰራ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር መዓረግ የሀረሪ ክልል ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ ገለፁ።
የሀረሪ ክልል ከተማ ልማት እና ክንስትራክሽን ቢሮ ከክልሉ ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመሆን በሀረር ከተማ አንደኛ መንገድ በሚከናወነው የኮሪደር መልሶ ልማት ስራ ላይ ከአካባቢው ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር መዓረግ የሀረሪ ክልል ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ የኮሪደር መልሶ ልማት ስራው የቅርሱን ታሪካዊ ይዘት ጠብቆ እንደሚከናወን በውይይቱ ገልፀዋል።
የኮሪደር መልሶ ልማት ስራው የአካባቢውን ኢኮኖሚ ሊያነቃቃ በሚያስችል መልኩ ታሪካዊ ይዘቱን ሳይለቅ ለነዋሪው በሎም ጎብኚዎች ምቹ እንዲሆን ዘመናዊ መሰረተ ልማቶችን አካቶ ተግባራዊ እንደሚሆንም አስገንዝበዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው ካሁን ቀደም በክልሉ ገቢራዊ የሆነው የኮሪደር ልማት የከተማውን የቀድሞ ምልከታ በመቀየር ውብ ገፅታን ያላበሰ መሆኑን በመጠቆም የመልሶ ልማት ስራውን እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።





0 Comments