የትምህርት ቤት ምገባ ማህበራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ አበርክቶው የጎላ ነው-ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ
ሐረር፤ የካቲት 25/2017 (ኢዜአ)፡-የትምህርት ቤት ምገባ ማህበራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ አበርክቶው የጎላ መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እ.ኤ.አ ከ2016 ጀምረው የአፍሪካ የትምህርት ቤት ምገባ ቀን በየዓመቱ እንዲከር በወሰኑት መሰረት ዘንድሮም 10ኛው የአፍሪካ የትምህርት ቤት ምገባ ቀን በሐረሪ ክልል ተከብሯል።
“አሥር የትምህርት ቤት ምገባ ዓመታት፤ ያለፈውን ስኬት እናክብር፤ መጪውን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው ቀኑ እየተከበረ የሚገኘው።
በመርሃ ግብሩ ላይ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ባስተላለፉት መልዕክት የትምህርት ቤት ምገባ ማህበራዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ አበርክቶው የጎላ ነው።
ትምህርት ለአንድ አገር እድገት መሰረት መሆኑን በመጠቆም በተለይ ጤናማ፤አምራች እና ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
የትምህርት ቤት ምገባ የመማር ማስተማር ሂደቱን ይበልጥ ውጤታማ በማድረግ፤የትምህርት ተሳትፎ እና ጥራትን ከማሳደግ ባለፈ የትምህርት ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝም አክለዋል።
በተለይ የትምህርት ቤቶች እና የተማሪዎች የትምህርት ቅበላን በማሳደግ አበርክቶው የጎላ መሆኑን በመጠቆም ድክመቶችን አርሞ ምገባውን ሳይቆራረጥ ጥራቱን ጠብቆ እንዲቀጥል በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።
መርሀ ግብሩን በራስ አቅም ለማከናወን ጥረት እንደሚደረግ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ ለመርሀ ግብሩ ቀጣይነት ማህበረሰቡ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ የትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ በበኩላቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ በማድረግ አበርክቶው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።
መንግስት በማህበራዊ ብልፅግና ለትምህርት ቤት ምገባ ትኩረት በመስጠት አገር አቀፍ የትምህርት ቤት ምገባ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ጊዜ ህብረተሰቡን በማስተባበር 4.5 ሚሊየን ተማሪዎች በተያዘው አመት ብቻ በትምርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አክለዋል።
በሐረሪ ክልል እየተካሄደ የሚገኘውን የትምህርት ቤት ምገባም አድንቀዋል።
የሐረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ ሀለፊ አቶ ጌቱ ነገዎ በበኩላቸው በክልሉ ከ38 ሺ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ምገባ መታቀፋቸውን ገልፀዋል።
የመርሀ ግብሩን ቀጣይነት ለማረጋገጥም አንድ ቁና ለአንድ ተማሪ በሚል መሪ ቃል ሀብት የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አክለዋል።
መርሀ ገብሩ የተማሪዎች የትምህርት መጠነ ማቋረጥን ከማስቀረቱም ባሻገር የተማሪዎች የትምህርት ቅበላን ማሳደግ መቻሉን አክለዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፤በትምህርት ሚኒስቴር አጠቃላይ የትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ እና በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ አመራሮችና የትምህርት ማህበረሰብ ተገኝተዋል።
በዕለቱ በከተማው በሚገኘው አንድ ሞዴል የ1ኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተካሄደ የሚገኘውን የተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር፤የዳቦ መጋገሪያ እና አንድ ቁና ለአንድ ተማሪ በሚል መሪ ቃል ከማህበረሸቡ እና አርሶ አደሩ የተሰበሰበውን ሀብት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።



0 Comments