Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

የተፋሰስ ልማት ስራ የክልሉን ምርትና ምርታማነት እያሳደገ ነው

በሐረሪ ክልል የሚከናወን የተፋሰስ ልማት ስራ የአካባቢ መራቆትን ከማሻሻል ባለፈ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ዑመር ተናገሩ።

በክልሉ በዘንድሮ በጋ ለሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ስራ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሮዛ ዑመር በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ አርሶ አደሩ የተፋሰስ ልማት ስራ ጠቀሜታውን በመረዳቱ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን ከዓመት ዓመት እያስፋፋ ይገኛል።

ባለፉት ዓመታት በክልሉ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የመሬት መራቆትን በመከላከል ለትውልድ የለማና አረንጓዴ አካባቢ ለማስረከብ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በክልሉ ቀደም ሲል በርቀት ተቆፍሮ ይገኝ የነበረው የከርሰ ምድር ውሃ በቅርበት እንዲገኝ ማስቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህም አርሶ አደሩ የመስኖ ልማት ስራውን በማጎልበት የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ከሚሰማው ይልቅ በተግባር የሚያየውን ነገር እንደሚቀበል ያነሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ፤ በአሁኑ ወቅት ከልማቱ የተሻለ ምርትና ገቢ እያገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ወይዘሮ ሮዛ ገለጻ በክልሉ በዘንድሮ ዓመት በ16 ተፋሰሶች ላይ ከ900 ሄክታር መሬት የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን ለማከናወን ታቅዷል።

በክልሉ ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ አራርሶ አደም በበኩላቸው በክልሉ የሚከናወኑ የተፋሰስ ልማት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ተረጂነትን እያስቀሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት የተለያዩ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራዎች እንደሚከናወኑ ጠቅሰው፤ ለዚህም አስፈላጊው የዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግባል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish