Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በፍጥነት አጠናቆ ወደ ስራ በማስገባት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ርብርብ ሊደረግ ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ

ሀረር፣ጥቅምት 18/2018(ሀክመኮ):-የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በፍጥነት አጠናቆ ወደ ስራ በማስገባት ማህበረሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ርብርብ ሊደረግ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በክልሉ የተጀመሩ፣አዳዲስ እና በመጠናቀቅ ሂደት ላይ የሚገኙ የልማት ስራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ ለማስቻል አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ አሳሰቡ።

በክልሉ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በተመለከተ ርዕሰ መስተዳድሩ ለአመራሩ በሰጡት የስራ አቅጣጫ የልማት ስራዎችን በማሳላጥ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በተለይ የደከር አጂፕ መንገድ ግንባታ ክልሉን በመሰረታዊ መልኩ የሚቀይር በመሆኑ በአጭር ግዜ ስራው ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት እንዲሆን ርብርብ ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ የአባድር ፕላዛ፣የላንድ ማርክ ፕሮጀክት የደከር ኮምቦልቻና የገንደፌሮ መንገድን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ይሰራል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ አዲስ የተያዙ የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራ፣የሀኪም ጋራ ኢንሼቲቭ እና ሌሎች ስራዎችን በፍጥነት ወደ ስራ ለማስገባት ይሰራል።

በጁገል ውስጥም በ 4 ሄክታር መሬት ላይ ሞዴል መንደር በመፍጠር ባለ 5 ኮኮብ ደረጃ ያላቸው ዘመናዊና ባህላዊ ገስት ሀውሶችን ለመፍጠር ይሰራል ብለዋል።

በሌላ በኩል ህገ-ወጥ ግንባታዎችን በመከላከል በኮሪደር ልማት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ለማስፋት ወረዳዎች ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

ለገጠር ኮሪደር ልማት ስራ መንገድን ሳይጨምር 100 ሚሊየን ብር ተመድቧል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በገጠር ወረዳዎች ሞዴል መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ይሰራል።

ከዚህም በተጨማሪ የገጠሩን ማህበረሰብ ኑሮ ለማሻሻል እና ለመደገፍ ትኩረት ተሰጥቷል በተለይ በምርት ስብሰባ ወቅት የምርት ብክነት እንዳይከሰት በማድረግ አርሶ አደሩ ምርቱን ለገበያ እስኪያቀርብ ድረስ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በቅዳሜ ገበያዎች አምራቹን ከሸማቹ ጋር በማገናኘት የዋጋ ንረትን ነማረጋጋት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ለትምህርት ጥራት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የመምህራን እጥረት እንዳያጋጥም ጥንቃቄ ከማድረግ ጀምሮ ትምህርት ቤቶችን ምቹ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር በአቦከር ወረዳ ከ 5 መቶ 45 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባውን ሞዴል ሀያስኩል ግንባታ መደገፍና መከታተል እንደሚገባም ገልፀዋል።

በሌላ በኩል የመጠጥ ውሃ ችግር እንዳይከሰት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ከፍሳሽ ማስወገጃ ሲስተሞች ጋር በተገናኘ በተለይ በጁገል ያለውን ችግር ለመቀረፍ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢንቨስትመንትን እንቅስቃሴዎችን ማበረታታትና መደገፍ፣የስራ ዕድል ፈጠራን ማበረታታት።
5 ሚሊየን ኮደርስ ስልጠና፣የፋይዳ መታወቃያ አገልግሎትን ማሳለጥ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በቀጣይ በአጭር ግዜ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስጀመር ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት ይሰራልም ብለዋል።

ሰላምና ፀጥታ ብሎም የህግ የበላይነትን በማስከበር የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ስራ ነው።

በመሆኑም ሰላምን ለማደፍረስ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ፀብ ቀስቃሽ የሆኑ የጥላቻ መልዕክቶችን የሚሰራጩ ሀይሎችን በህግ ተጠያቂ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish