የሹዋሊድ ክብረ በዓል ሰላምን፣ አብሮነትን እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ ይከበራል፦ የሀረሪ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን
ከቀናት በኋላ የሚከበረው የዘንድሮው የሹዋሊድ ክብረ በዓልን በማስመልከት ከሀረሪ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ፦
የሹዋሊድ ክብረ በዓል በሀረሪ ብሄረሰብ ዘንድ ለምዕተ አመታት ሲከበር የኖረና በትውልድ ቅብብሎሽ ባህሉንና ወጉን ጠብቆ ከነክብሩ ዛሬ ላይ የደረሰ ባህላዊ በዓል ነው።
የሀረሪ ህዝብ ልዩ መገለጫ እሴት የሆነው የሹዋሊድ በአል ከበዓልነቱ ባሻገር የሀረሪ ህዝብ ጥልቅ የሆነ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ እሴቶች መገለጫም ነው።
የበዓሉ አከባበር የሀገራችን ሕዝቦች የአብሮነት ዕሴትን እያጎለበቱ ከሚገኙ ባህላዊ በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን በተለይም በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የባህል ትውውቅ በመፍጠር የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከር በኩልም ገንቢ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የሹዋሊድ በዓል አከባበር ከህዳር 25 /2016 ጀምሮ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ አለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል።
በመሆኑም በዓሉ የሀረሪ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያውያን ከዚያም አልፎ የዓለም ህዝቦች ሁሉ ሃብት ሆኖ ይገኛል።
ሹዋሊድ በተለይም የክልላችን ብሎም የሀገራችን የቱሪዝም ዘርፍ እንዲጎለብት ከማድረግ አንፃር የላቀ ጠቀሜታ ያለው በዓል ነው።
ዘንድሮ የሚከበረው የሸዋል ኢድ በአል “ቅርስ ሕብቶቻችን ለቱሪዝም ልማታችን” በሚል መሪ ሀሳብ በድምቀት ይከበራል።
የዘንድሮው የሹዋሊድ በዓል አከባበርም ሰላምን፣ አብሮነትን እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
በበዓሉም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እና አጎራባች ክልሎች በሐረር ከተማ የባህል፣ ፌሲቲቫልና አውደ ርዕይ፣ የልማት ስራዎች ጉብኝትን ጨምሮ ሌሎች መርሃግብሮች የሚካሄድ ሲሆን በበዓሉ ላይም ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚመጡ እንግዶች ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የሀረሪ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት
መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ. ም
ሐረር
0 Comments