የሰው ሰራሽ አስተውሎት የመጪውን ዓለም መጻዒ ዕድል የሚወስን በመሆኑ ወጥ እሳቤ ይዘን መስራትና መከተል አለብን- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
የሰው ሰራሽ አስተውሎትና መሰል የዘመኑ ቴክኖሎጂዎች የመጪውን ዓለም መጻዒ ዕድል የሚወስኑ በመሆኑ ወጥ እሳቤ ይዘን መስራት መከተልና በሰው ሃይል ልማት ላይ በትኩረት መስራት አለብን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮችና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ዓለም በአዳዲስ ፈጠረና ቴክኖሎጂ ዘርፎች በማይገመት ፍጥነት እየተለወጠ ነው ብለዋል።
ለአብነትም በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በኮኔክቲቪቲ፣ በባዮ ምህንድስና፣ በስፔስ ቴክኖሎጂ እና መሰል የዘመን ስልጣኔ በፍጥነት እየተራመደ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ፍጥነት ጋር ትውልዱ እንዲራመድ ለማድረግ በዘመኑ ቴክሎኖጂዎች ሽግግር ላይ መስራት ይገባል ብለዋል።
ለአብነትም የሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ ልማዳዊ የሰው ልጅ አካሄዶችን ሙሉ በሙሉ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየተኩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ስጋት ተገንዝቦ ነገን ታሳቢ ያደረገ ስራ መስራት እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
የዓለም ፍጥነት እጅግ አስፈሪ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመኑን በዋጁ የሰው ሰራሽ አስተውሎትና መሰል ቴክኖሎጂዎች ላይ ካልሰራን በምርት ተወዳዳሪ ሆኖ መቀጠል አይቻልም ብለዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት እና መሰል የዘመኑ ቴክኖሎጂዎች የመጪውን ዓለም መጻዒ ዕድል የሚወስኑ በመሆኑ ወጥ እሳቤ ይዘን መከተልና በሰው ሃይል ልማት ላይ በትኩረት መስራት ይጠበቅብናልም ነው ያሉት
በሰው ሰራሽ አስተውሎትና መሰል የዘመኑ ቴክኖሎጂዎች ላይ ልጆች መሰረታዊ ዕውቅት እንዲይዙ ነገን ማየትና በቴክኖሎጂ ላይ ወጥ እሳቤ ይዞ መከተል ያስፈልጋልም ብለዋል።
በመሆኑም ከጥርጣሬና ሽኩቻ ይልቅ የሀገርን አንድነት ማጽናት የሁላችንም የጋራ አቋም አድርገን መስራት አለብን ሲሉ አስገንዝበዋል።

0 Comments