Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

የሐረሪ ቋንቋ፣ ባህል እና ቅርስ ጥበቃ ላይ የተሰሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ -ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ሀረር ሀምሌ 15/2016 (ሀክመኮ) በ2016 ዓመት የሐረሪ ቋንቋ፣ ባህል እና ቅርስ ጥበቃን በማጎልበት የተከናወኑ ውጤታማ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ ስድስተኛ ዙር ሶስተኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔውን በዛሬው ዕለት አካሂዷል ።

የሀረሪ ጉባኤ ፣የክልሉ ትምህርት ቢሮ እና የባህል ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ የ2016 ዓመት የስራ አፈፃፀማቸውን በጉባዔው ላይ አቅርበዋል።

በጉባኤው ላይ በበጀት ዓመቱ በክልሉ በባህል፣ ቅርስና በሐረሪ ቋንቋ ጥበቃና የማጎልበት ስራዎች በሰፊው መከናወናቸው ተመላክቷል።

በተለይ የጁገል ዓለም አቀፍ ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎች፣ የባህል እሴቶችን የመጠበቅና የማበልፀግ ስራዎች፣ በዓመቱ የባህላዊና ታሪካዊ ሥነ ሥርዓቶችና በዓላት ነባር ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲካሄዱ ከማድረግ አንፃር የተደረጉ የክትትል እና ድጋፍ ስራዎች በመድረኩ ላይ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት በ2016 ዓመት የሐረሪ ቋንቋ፣ ባህል እና ቅርስ ጥበቃን በማጎልበት የተከናወኑ ውጤታማ ስራዎች በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በተለይ ዓለም አቀፍ ቅርስ የሆነው የሹዋሊድ በዓል በማይዳሰሱ ቅርሶች በአለም አቀፍ ደረጃ መመዝገቡ ብሎም የሐረሪ ቋንቋን ከማሳደግና ደረጃን ከማሻሻል አንፃር የተዘጋጁ የትርጉም መተግበሪያዎች አበረታች መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

የጉባኤው አባላት በበኩላቸው በቀረበው ሪፖርት ላይ በሰጡት አስተያየት በበጀት አመቱ በዘርፉ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አረጋግጠዋል።

የተጀመሩ ስራዎች ግለታቸውን ጠብቀዉ ሊከናወኑ ይገባል ያሉት አባላቱ በተለይ ጉባዔው አስፈፃሚ ተቋማት ያካሄዷቸውን ተግባራት ከመከታተል አንፃር ጥሩ የሚባል ክትትል ዕና ድጋፍ ማድረጉን በመጠቆም የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ጉባዔው በክልሉ ህገ መንግስት የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር መሠረት በማድረግ በይበልጥ ጠንካራ ህግ ማውጣትና የክትትል ስራዎችን መስራት እንደሚገባም ተነስቷል።

የቀረቡ ሪፖርቶች ላይ ጉባዔው ከመከረ በኋላ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

በተጨማሪም የ2017 ዓመት የሀረሪ ጉባዔ ፣ የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ እና የክልሉ ባህል ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ ዕቅድ ቀርቦ በአባላቱ አስተያየት ከተሰጠበትና ከተመከረበት በኋላ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish