የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) የ2018 በጀት አመት ረቂቅ በጀት ከ7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሆን ወሰነ
የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) የ2018 ዓ.ም የክልሉ መንግሥት ረቂቅ በጀት ከ7 ቢሊዮን 476 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሆን ውሳኔ አሳተላልፏል፡፡
ካቢኔው በክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ የቀረበለትን የ2018 የበጀት አመት ረቂቅ በጀት መርምሮ በማፅደቅ ለክልሉ ምክር ቤት መርቷል።
በዚህም መሰረት በክልል ደረጃ ከተያዘው በጀት 61 በመቶ ለካፒታል በጀት የተመደበ ሲሆን 37 በመቶው ደግሞ ለመደበኛ በጀት የሚውል ነው ተብሏል።
የበጀቱ ምንጭም በዋናነት በክልሉ ከተለያዩ ገቢዎች የሚሰበሰብ ገቢ እንዲሁም ከፌዴራል መንግሥት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመር ለክልሎች የሚሰጥ ድጎማና ከሌሎች ምንጮች ታሳቢ መደረጉን ተገልጿል።
በጀቱ ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀርም የ28 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ነው የተገለፀው።
በዚህ ወቅትም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንዳሉት በ2017 የበጀት አመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁና ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ስራ ትኩረት ይሰጣል።
የግብርና ልማት ስራዎችን ማጠናከርና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት የሚያስችሉ ስራዎች ታሳቢ ተደርጓል ብለዋል።
በተለይም በገጠርና ከተማ የሕዝብን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ሊመልሱ በሚችሉ ተግባራት ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ነው ያመላከቱት።
ለገጠር ኮሪደር ልማት ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።
በጀቱ ቁጠባን መሰረት በማድረግ በተለይም የህዝቡን ህይወት በሚያሻሽሉና መሰረታዊ ጥያቄ በሚመልሱ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማስቻል አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።
በድህነት ቅነሳ እንዲሁም ለዜጎች የስራ እድል ፈጠራ ማጎልበት ላይ ትኩረት በመስጠት ርብርብ እንደሚደረግም አመላክተዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ ለማስጀመር ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ያመላከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ በዚህም ለህብረተሰቡ ፈጣን፣ ፍትሃዊና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።
በክልሉ ገቢን አሟጦ ከመሰብሰብ አንፃር በትኩረት መንቀሳቀስ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የክልሉ ኢኮኖሚ በሚያመነጨው ልክ በታቀደው ልክ መሰብሰብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ምክር ቤቱም በቀረበው የ2018 ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ነው ወደ ክልሉ ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ የወሰነው።

0 Comments