Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

ዘመናዊ እና ወጪ ቆጣቢ የትራንስፖርት ሲስተሞችን እውን ለማድረግ ይሰራል-አቶ ኦርዲን በድሪ

በሀረሪ ክልል ዘመናዊ እና ወጪ ቆጣቢ የትራንስፖርት ሲስተሞችን እውን ለማድረግ እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

የሀረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በክልሉ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ትራንስፖርትን ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከስዊፍት ቴክኖሎጂ አቅራቢዎች ጋር ተወያየ።

በውይይቱ ላይ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደገለፁት ከተማዋን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን ትኩረት ተሰቶ እየተሰራ ነው።

በተለይ በክልሉ ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ትራንስፖርትን ማሳለጥ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን አስገንዝበዋል።

ተሽከርካሪዎቹ ወጪ ቆጣቢ መሆናቸው ማህበረሰቡ ከትራንስፖርት አቅርቦት ጋር በተያያዘ እያቀረበው የሚገኘውን ቅሬታ ለመፍታት የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።

በሀረር ከተማ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ከተማውን የማይመጥን መሆኑን በማመላከት ወጪ ቆጣቢ እና ለአየር ንብረቱ ተስማሚ እና ምቹ የሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን አገልግሎት ለማስጀመር እንደሚሰራ ገልፀዋል።

የትራንስፖርት ሲስተሙ የክልሉን ቱሪዝም መዳረሻዎች ታሳቢ ያደረገ ለአካባቢው ተስማሚ መሆኑ የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ የሚያጎለብት መሆኑንም ጠቁመዋል።

የስዊፍት ቴክኖሎጂ ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ አሸብር በበኩላቸው ቴክኖሎጂው ከተማዋን ለማዘመን እና የስራ ዕድልን ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል።

በተለይ ለነዳጅ ግዢ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ አገር ውስጥ ለማስቀረት የሚረዳ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ድርጅቱ በክልሉ ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ ለማድረግ የሚያስችሉ ጣቢያዎችን ለመገንባት ፍላጎት እንዳለውም ገልፀዋል።

በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ግለሰቦች በ8 ዓመት የሚከፈል የብድር አቅርቦት እንደሚመቻችም ጠቁመዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish