ዘመኑ በታሪካችን በጉልህ የሚነሳ አዲስ ምዕራፍ የተጀመረበት ነው – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
ዘመኑ በታሪካችን በጉልህ የሚነሳ አዲስ ምዕራፍ የተጀመረበት ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለፁ።
6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።
በንግግርቸውም በአዲሱ ዓመት መባቻ የበርካታ ዓመታት ቁጭታችንና የጥረታችን ውጤት የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ያስመረቅንበት ነው ብለዋል።
መስከረም ወር የኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ሃብት የብስራት ጅማሮ የሆነውን የተፈጥሮ ጋዝ ያወጣንበት ነው ሲሉም ገልፀዋል።
የተፈጥሮ ሃብታችንን በመጠቀም የእድገታችን መልህቅ የሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የተመረቁበት መሆኑን አመልክተው፤ ዘመኑ በታሪክ በጉልህ የሚነሳ አዲስ ምዕራፍ የተጀመረበት ነው ብለዋል።
የኢኮኖሚ ለውጡ መሰረቶች ያሉንን አቅሞች ማወቅ፣ በችግር ውስጥ እድልን ማየት፣ በፈጠራና በፍጥነት እንዲሁም በትብብር የተለያዩ አቅሞችን በማሰባሰብ ዘላቂ ግቦችን በማሳካት ላይ ያተኮሩ መሆናቸውንም አመላክተዋል።
እነዚህ መሰረቶች አጠቃላይ ሀገራዊ እድገትን ማረጋገጥ ማስቻላቸውን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ከዝናብ ጥገኝነት ወደ ራስ ቻይ አምራችነት በመብቃት፣ የማዕድን ሃብታችንን ወደ ወሳኝ የሃብት ምንጭነት በመቀየር፣ የቱሪዝም ሃብትን ወደ ጉልህ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽነት በማሳደግ የህዝብን አኗኗር በመለወጥ እና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ስኬት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በዚህ መሰረት በ2017 በጀት ዓመት ኢኮኖሚው ዘጠኝ በመቶ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

0 Comments