“ከተረጂነት ለመላቀቅ እና ምርታማ ለመሆን በተግባር የሚገለጽ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል”- አቶ ጌቱ ወዬሳ
ከተረጂነት ለመላቀቅ እና ምርታማ ለመሆን የአመራሩና የህብረተሰቡ በተግባር የሚገለጽ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ሲሉ የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ ተናገሩ።
በሀረሪ ክልል ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በሚል ቃል ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ ያለመ የንቅናቄ መርሃግብር ሲካሄድ መቆየቱ የተገለፀ ሲሆን ላለፉት ሶስት ወራት ሲካሄድ የቆየው ንቅናቄ እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው ማህበረሰብ ተሳታፊ ማድረግ መቻሉ ተጠቁሟል።
ንቅናቄውን አስመልክተው የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳ እንዳሉት በክልሉ በተደረገ ንቅናቄ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማወያየት በተረጂነት አሰተሳሰብ ያለውን ተጽእኖ በዝርዝር በማቅረብ መግባባት ላይ ተደርሷል።
ይህም ከተረጂነት ወደ ልማት ለማሸጋገር ትልቅ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲታይ አስችሏል።
በራስ አቅም ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን የመደገፍ ስራ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ከድህነት ለመላቀቅ በራስ አቅም መደጋገፍን ማሳደግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
የተጀመሩ ስኬታማ ስራዎችን በማጽናትና ጉድለቶችን በማረም የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በክልሉ የተቀናጀ ግብርናን በመከወን በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ኃላፊው ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ከልመና ወደ ልዕልና በሚል እሳቤ የተጀመረውን ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ለማሳካት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባም አስረድተዋል።
ከተረጂነት አስተሳሰብ ለመላቀቅ እና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተጀመረው ንቅናቄ የሀይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎችም የማህበረሰብ አደረጃጀቶች በአስተሳሰብ ቀረጻ በኩል ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ከተረጂነት መውጣት ብሔራዊ ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
ከተረጂነት ለመላቀቅ እና ምርታማ በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ በተለይም የአመራሩ እና የህብረተሰቡ በተግባር የሚገለጽ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በ2017 የአንደኛው ሩብ አመትም በከተማና በገጠር የሚገኙ ተረጂዎችን ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር በዋናነት ከግብርና ልማት ኢኒሸቲቦች እና ከከተማ አማራጭ የስራ እድል ፈጠራ ጋር የማቀናጀት ስራ ስለመከናወኑ ጠቁመዋል።
ህዝቡን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።
0 Comments