Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

ከተማውን ለነዋሪው ብሎም ለጎብኚዎች የተመቸ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው:- ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ

ሀረር ሀምሌ 11/2016(ሀክመኮ):- የሀረር ከተማን ለነዋሪው ብሎም ለጎብኚዎች የተመቸ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ከከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ጋር በመሆን የክረምት በጎ ፈቃድ ስራን አስጀምረዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በክልሉ ለ 5 መቶ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ፤ ለከተማ ውበት የሚሆን ችግኞች እና በክልሉ ለተጀመሩ የከተማ ልማት ስራዎች የሚውል 20 ሚሊየን ብር ድጋፍ አበርክቷል።

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በመርሀ ግብሩ ላይ እንደገለፁት አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዘርፉን የሚያጠናክሩ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል።

በተለይ በሀረር ከተማ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ ከተማዋን የሚመጥን ዕድገት በማስመዝገብ ለነዋሪው ብሎም ለጎብኚዎች የተመቸች ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ለከተማው ፅዳት እና ውበት ብሎም ለአረንጓዴ አሻራ የተሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ ከማስቀጠል ጎን ለጎን ከተማው በፕላን እና ስርዓት እንዲመራ ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር እየተሰራ እንደሚገኝም አክለዋል።

በሌላ በኩል በክልሉ የበጎ ፈቃድ ተግባር በተሻለ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።

በበጎ ፈቃድ ተግባሩ ተማሪዎችን በትምህርት ቁሳቁስ ፤አረጋውያንን መኖሪያ ቤታቸውን በማደስ የመደገፍ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ በማመላከት መሰል ተግባራት ተጠናክረው የሚቀጥሉት የሁሉም አበርክቶ ሲኖር መሆኑን አስገንዝበዋል።

የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚነስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው በቀድሞው አተያይ ከተሞችን የገጠሩ ጥገኛ አድርጎ የማሰብ ዝንባሌዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

የለውጡ መንግስት ይህን መሰሉን ምልከታ በማስቀረት ለከተሞች ዕድገት ፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፍ በማውጣት በመሰረተ ልማት ዘርፍ መነቃቃት እንዲፈጠር ማስቻሉን ገልፀዋል።

በዚህም በሀረሪ ክልል ለመኖሪያ ብቻ ሳይሆን ለስራም ጭምር የተመቹ ከተሞቸን ለመፍጠር በተኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ መመልከታቸውን ገልፀዋል።

በክልሉ በከተማ ልማት ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ከተማዋና ህዝቡን የሚመጥኑ በተለይ ከነዋሪው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በክልሉ የተከናወኑ የአረንጓዴ ልማት እና የጀጎል መልሶ ልማት ስራዎች ለነዋሪው ፈታኝ የነበሩ አካባቢዎች እንዲፀዱ በማድረግ ሰዎች ተቀምጠው የሚጨዋወቱባቸው ንፁህ እና በብርሀን የተሞሉ እንዲሆኑ አስችሏል ብለዋል።

በተለይ አለም አቀፉ የጁገል መልሶ ልማት ስራ ለሌሎች ከተሞች በአርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል የክረምት በጎፈቃድ አመት ጠብቆ የሚከናወን ሳይሆን አመቱን በሙሉ ሊተገበር የሚገባ የሁልጊዜ ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በክልሉ ለሚገኙ 500 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ፣ለክልሉ የአረንጓዴ ልማት ስራ የሚውሉ ችግኞችን እንዲሁም በከተማው ለተጀመሩ የልማት ስራዎች 20 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማበርከቱንም ሚኒስትሯ ገልፀዋል።

በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን የተመለከቱ ሲሆን የክልሉ በርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish