Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

ኢትዮ-ቴሌኮም በኢትዮጵያ የዲጂታል ግብይት ሥርዓት እንዲጠናከር ገንቢ ሚና እየተጫወተ ነው  

ኢትዮ-ቴሌኮም በኢትዮጵያ የዲጂታል ግብይት ሥርዓት እንዲጠናከር ገንቢ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት በተነሱላቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እንዲሁም ቀጣናዊ፣ አሕጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የቱሪዝምና የአገልግሎት ዘርፍ በ7 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ብለዋል።

የቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፉም እያስመዘገበ በሚገኘው አመርታዊ ለውጥ ከአዲስ አበባ ባሻገር በክልል ከተሞችም ከኤልቲኢ፣ 4ጂ ወደ 5ጂ የማስፋፋት ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።

የሞባይል ገንዘብ የማስተላለፍ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ይገኛል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮ-ቴሌኮም ከማገናኘት አልፎ በኢ-ኮሜርስ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚጫወት ተቋም ሆኗል ብለዋል።

የዲጂታል ግብይት ሥርዓትንም እንደዋና ሥራው አድርጎ በመሥራቱ ለኢትዮጵያ የዲጂታል ግብይት ገንቢ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አንስተዋል።

ከቴሌኮም በተጨማሪም የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ትርፋማ መሆን ተስኗቸው አብዛኞቹ በድጎማ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የመንግሥት ኩባንያዎችን ትርፋማ ማድረግ እንዳስቻለ አብራርተዋል።

በተሰራ የለውጥ እርምጃም ሁሉም ባይባልም በርካታዎቹ እዳቸውን በመክፈል ትርፋማ እንዲሆኑ ማድረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በታለመለት አግባብ ድጋፍ እያገኘ መጓዝ ከቻለ በመንግሥት ሥም የተቋቋሙ ትልልቅ ኩባንያዎችን ትርፋማ እንዲሆኑ ያግዛል ብለዋል።

የካፒታል ማርኬትም ብዙ ሃብትና ዕውቀት በመሰብሰብ ብዙ ዜጎች በኮርፖሬት ፋይናንስ ሥርዓት ኢንቨስት አድርገው የመንግስትን የፋይናንስ ሥርዓቱን በሕግ ብቻ እንዲያስተዳድር በእጅጉ እንደሚያግዝ አንስተዋል።

የኢትዮ-ቴሌኮም የ10 በመቶ ድርሻ አክሲዮን ሽያጭ ይፋ መደረጉን አስታውሰው፤ በተቀሩት የመንግሥት ኩባንያዎችም መሰል ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish