Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

ኢትዮጵያ መለመን የለባትም፤ልጆቿ ተግተው ሰርተው ከልመና ራሳቸውን መገላገል አለባቸው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

ኢትዮጵያ መለመን የለባትም፤ልጆቿ ተግተው ሰርተው ከልመና ራሳቸውን መገላገል አለባቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፥ አምርታ መብላት የማትችል ሀገር ብሄራዊ ጥቅሞቿን ለማሳካት እንድምትቸገር ገልጸዋል።

ምርት ከማምረት እና ከመሸጥ ባለፈ በግብርና እሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ጉዳዮች ላይ ሁሉን አቀፍ መፍትሄ ማምጣት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማምጣት ያስችላል በሚል እሳቤ ሲከናወኑ የቆዩ ስራዎች ውጤት ማስገኘታቸውን አመልክተዋል።

ባለፉት ዓመታት 27 ሚሊዮን ዜጎች በሴፍቲኔት ኢኒሼቲቭ በተረጂነት ማዕቀፍ ውስጥ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

መንግስት ዜጎችን ከሴፍቴነት ነጻ ለማውጣት በግብርናው ንዑስ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሲሰሩ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በምስራቅ ሐረርጌ እና በደቡብ ሃላባ በነበራቸው ቆይታ አርሶ አደሮች ከሴፍቲኔት ተላቀው በራሳቸው አቅም ማምረት መጀመራቸውን እንደተመለከቱ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ መለመን የለባትም ልጆቿ ተግተው ሰርተው ከልመና ራሳቸውን መገላገል አለባቸው የሚለው እምነት ፍሬ እያፈረ መምጣቱን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

ዘንድሮ 23 ሚሊዮን ዜጎች ከሴፍቲኔት ተረጂነት ነጻ ወጥተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህ የማንሰራራት እና ኢትዮጵያ ከጥገኝነት ለመላቀቅ የጀመረችው ስራ ትልቁ ማሳያ ነው ብለዋል።

በቀጣይ የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ የጋራ ጥረት እና ርብርብ እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish