Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

አጠቃላይ በጀታችን ለድህነት ቅነሳ ትኩረት ያደረገ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አጠቃላይ በጀታችን ለድህነት ቅነሳ ትኩረት ያደረገ ነው፤ ከዚያ የተረፈው ለዕዳ ክፍያ እና ድጎማ ለሚያስፈልጋቸው የሚውል ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2018 በጀት ትኩረትና የቀጣይ ዓመት ሀገራዊ ዕድገትን በተመለከተከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም አጠቃላይ በጀታችን ለድህነት ቅነሳ ትኩረት ያደረገ ነው፤ ከዚያ የተረፈው ለዕዳ ክፍያ እና ድጎማ ለሚያስፈልጋቸው የሚውል ነው ብለዋል።

አብዛኛው ገንዘባችን ድጎማ፣ ዕዳ ክፍያና መሰል ጉዳዮችን ስለሚያካትት የካፒታል በጀታችን ዕድገት ቢኖረውም ውስን ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በአንድ በኩል የኑሮ ውድ ሆነ ደሞዝ ችግር ሆነ እያልን እሱን ሳንመልስ በውስን ገቢ ያገኘውን ገቢ በሙሉ ልማት ላይ ካዋልን ችግሩ ስለሚባባስ ያንን እያስታረቁ መሄድ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የእኛ ዕድገት መታየት ያለበት ስንት ኩንታል እንደጨመርን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም እንደነበረው የቁጥር ሳይሆን ጥራት ያለው ዕድገት እያስመዘገበች ነው ብለዋል።

ይህም የሚታይ ዕድገት ነው ካሉ በኋላ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሚቀጥለው ዓመት የበለጠ ትልቅ ውጤት ያስመዘግባል ሲሉም ገልጸዋል።

ያ እንዲሆን ግን ሁሉም ዝቅ ብሎ አፈር እየነካ በትጋት በመስራት፣ ህዝብን በማስተባበር፣ ሌብነትን በመቀነስ፣ በውጤት ማመን፣ ጀምሮ በመጨረስ፣ የኢትዮጵያን ማንሰራራት የሁላችንም እምነት በማድረግ ልማትና ዕድገት ይመጣል ብለዋል።

ኢትዮጵያ እያደገች ነው፤ ኢትዮጵያ እያንሰራራች ነው፤ ኢትዮጵያ አቧራዋንና እዳዋን እያራገፈች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የበለፀጸገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን እናስረክባለን ነው ያሉት።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish