አምርታ መብላት ያልቻለች ሀገር ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማረጋገጥ ትቸገራለች በሚል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ግብ ይዘን ሰርተናል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አምርታ መብላት ያልቻለች ሀገር ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማረጋገጥ ትቸገራለች በሚል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ግብ ይዘን ሰርተናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ግብርናን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋልታ መሆኑንና የወጪ ንግድ ገቢያችን ዋልታም ነው ብለዋል።
ግብርና በርካታ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚሳተፍበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ትልቅ ስፍራ እንዲሰጠው ያደርጋል ነው ያሉት።
ግብርና ቢዚህ ዓመት 6 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት እንዲያመጣ ነው የታቀደው ሲሉ ገልጸው የግብርናው ዘርፍ ከሌሎች ዘርፎች ልዩ ትኩረት ያገኘው ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት ማግኘት አለባት፤ አምርታ መብላት ያልቻለች ሀገር ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማረጋገጥ ትቸገራለች በሚል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ግብ ይዘን ሰርተናል ብለዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት 27 ሚሊዮን በሴፍቲኔት የተያዙ ዜጎች ነበሩ፤ እነዚህን ከሴፍቲኔት ለማሸጋገር ሲሰራ ቆይቷልም ነው ያሉት።
በዚህም ለረጅም ዘመናት በሴፍቲኔት ሲተዳደሩ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ወደ መተዳደር ተሸጋግረዋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም 23 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ከሴፍቲኔት ተረጂነት ነጻ ወጥተዋል ሲሉም ተናግረዋል።
ይህ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ማሳያ ስለሆነ ኩራት ሊሰማን ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀሪው ከ4 ሚሊዮን ያላነሰ ተረጂን ነጻ በማውጣት ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ የምግብ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች ሀገር ማድረግ አለብን ለዚህም ሰፊ የሚታረስ መሬት አለን ነው ያሉት።

0 Comments