Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

አለም አቀፉ የጁገል ቅርስ መልሶ ልማት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር አድርጓል-አፈጉባኤ አቶ ሙህየዲን አህመድ

ሀረር ታህሳስ 24/2017(ሀክመኮ):-አለም አቀፉ የጁገል ቅርስ መልሶ ልማት ስራ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ማድረጉን የሀረሪ ጉባኤ አፈጉባኤ አቶ ሙህየዲን አህመድ ገለፁ።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከሐረሪ ክልል ባህል ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ በመተባበር በጁገል ዓለም ዓቀፍ ቅርስ አስተዳደር፣ ጥበቃና ዘላቂ ልማት ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሀረሪ ጉባኤ አፈ ጉባኤ አቶ ሙህየዲን አህመድ በአለም አቀፉ የጁገል ቅርስ የተከናወነው የመልሶ ልማት ስራ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር  ማድረጉን ገልፀዋል።

አቶ ሙህየዲን አክለውም የጁገል ዓለም ዓቀፍ ቅርስን ለነዋሪውና ለጎብኚው ምቹ ለማድረግ የተከናወነው ስራ የተመዘገቡ ውጤቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት ኅብረተሰቡን በማስተባበር እያከናወነው ያለው ሥራ አበረታች ከመሆኑ ባለፈ ለሌሎች አካባቢዎችም ልምድ የሚቀሰምበት መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከተመዘገቡት ቅርሶች መካከል የጁገል ዓለም ዓቀፍ ቅርስ አንዱ መሆኑንም አውስተዋል።

የሰው ልጆች የጋራ ኃብት የሆነውን ቅርስ ከሚደርስበት አደጋ ለመታደግ የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፤ የጁገል ዓለም ዓቀፍ ቅርስን በመጠበቅ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

ባለሥልጣኑ የጁገል ዓለም ዓቀፍ ቅርስን የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራ እና ነዋሪው ከቅርሱ ተጠቃሚ እንዲሆን እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ በበኩላቸው ከጁገል ዓለም ዓቀፍ ቅርስ በተጨማሪ በክልሉ የሚገኙ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶችን የመንከባከብና የመጠበቅ ሥራዎች በሰፊው መከናወናቸውን ገልጸዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish