ባለፉት አምስት ዓመታት የልማት እና መልካም አስተዳደር ጥያቄያችን ምላሽ እያገኘ ነው -የሀረር ከተማ ነዋሪዎች
በሀረሪ ክልል ባለፉት አምስት አመታት ለዘመናት ስናፍቀርበው የነበረው የልማት እና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ ነው ሲሉ የሀረር ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።
ባለፉት አምስት አመታት በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ስራዎች የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ እና ምቹ የመኖሪያ እና ማረፊያ ስፍራዎችን የፈጠሩ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።
በተለይ በክልሉ ካሁን ቀደም የነበሩ መንገዶች ለእግረኞች እንቅስቃሴ እምብዛም ያልተመቹ እና ለአደጋ የሚያጋልጡ በመሆናቸው የቅሬታ ምንጭ እንደነበሩ አስታውሰው አሁን ላይ ችግሩ መቀረፉን ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም በከተማው ሲስተዋል የነበረው የጽዳት ጉድለት ችግር ተቀርፎ ምቹ እና ውብ የእግረኛ መንገዶች እና አካባቢዎች መፈጠራቸውን ገልገዋል።
በክልሉ ገቢራዊ እየሆኑ በሚገኙ የኮሪደር ልማት ስራዎችም ማህበረሰቡ የስራ ዕድል ተጠቃሚ እየሆነ እንደሚገኝ አክለዋል።
በተለይ በአለም አቀፉ የጁገል ቅርስ በኮሪደር ልማቱ የተከናወነው የመልሶ ልማት ስራ ስፍራውን ለጎብኚዎች ብሎም ነዋሪው የተመቸ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።
ይህም የቱሪስቶች ፍሰቱን ከማሳደጉ ባሻገር ቆይታቸውን በማርዘም ከዘርፉ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያስቻላቸው መሆኑንም ገልፀዋል።
በተለይ በክልሉ የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት በከተማ እና ገጠር ፍትሀዊ በሆነ መልኩ በተገነቡ ትምህርት ቤቶች ልጆቻቸውን በአቅራቢያ ማስተማር መቻላቸውን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል መንግስት በግብርናው ዘርፍ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ ብሎም የደላሎችን ጣልቃ ገብነት በማስቀረት አምራቹን ከሸማቹ ጋር በማገናኘት የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ ያከናወናቸው ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን አንስተዋል።
በተለይም በቅዳሜ ገበያ እየቀረበ ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህዝቡ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን በመጠቆም የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።
ባለፉት አምስት አመታት እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ማሸጋገር እንደሚቻል ተስፋ የሰጡ መሆናቸውንም ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።




0 Comments