በደም ፣በባህል እና በታሪክ የተጋመድን ህዝቦች በመሆናችን አብሮነትን ማጎልበት ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
ሀረር ፤ሐምሌ 04/2016 (ሀክመኮ);-ኢትዮጵያዊያን በደም ፣በባህል እና በታሪክ የተጋመድን ህዝቦች በመሆናችን አብሮነትን ማጎልበት ይገባል ሲሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የ26ኛው ዓለም አቀፍ የሐረር ቀን በዓል አካል የሆነው የአብሮነት ቀን ዛሬ ተከብሯል።
በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፤ “ኢትዮጵያዊያን በታሪክ ከመቆራኘት ባለፈ የጋራ እሴት፣ ባህል፣ አኗኗር እና ወግ ያለን ህዝቦች ነን” ብለዋል።
እንዲሁም በደም፣ በባህል፣ በታሪክና በሌሎች የተጋመድን ህዝቦች በመሆናችን አብሮነትን ማጎልበት ይገባል ብለዋል።
የአብሮነታችን መሰረት ትውልድ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ትውልዱ መገለጫችን የሆነውን የአብሮነት ባህል አበልጽጎ ለመጪው ትውልድ ሳይሸራረፍ ማስረጽ እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል።
አንድነት እና አብሮነትን የሚጎዱ የጥላቻ፣ የተዛቡና ሌሎች ትርክቶችን መከላከልና ኢትዮዽያዊነትን የሚገነቡ ትርክቶችን ማጉላት ይገባልም ብለዋል።
የክልሉ ህዝብ መገለጫ የሆነው የሰላም፣ አብሮነትና መቻቻል እሴቶች ሳይሸራረፉና ሳይሸረሸሩ በጠንካራ አለት ላይ እንዲገነቡ መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
በክልሉ እየተከናወነ የሚገኘው ልማት ፍትሃዊ፣ ሁሉንም ያማከለና ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ኦርዲን፤ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የክልሉ መገለጫ የሆነውን የአብሮነት እሴት በማጠናከር የተጀመሩ የልማት ሰራዎችን ማጎልበት ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው የአብሮነት ቀን ሐረር የምትታወቅበትን የሰላም፣ የመቻቻልና የአብሮነት እሴት ለማስቀጠልና ለትውልድ ለማስተላለፍ ጠቀሜታው የጎላ ነው።
ለአብሮነት ትኩረት መሰጠቱ እርስ በርስ ለመተባበር፣ ለመረዳዳት እና አንድነትን ለማጠናከር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን በማከል።
በክብረ በዓሉ ላይ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ የሀረሪ ብሄራዊ ጉባኤ አፈ ጉባኤ አቶ ሙሕየዲን አህመድ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመርን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የአመራር አባላት፣ የአገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች፣ የህብረተሰብ ተወካዮች እንዲሁም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተገኝተዋል።




0 Comments