በዘንድሮው ዓመት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚጠጋ የውጭ ቱሪስት ኢትዮጵያን ጎብኝቷል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
በዘንድሮው ዓመት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚጠጋ የውጭ ቱሪስት ኢትዮጵያን መጎብኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አገልግሎት ዘርፉ ላይ በተቀናጀ መልኩ መስራት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ የመሸከም አቅም ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በዘንድሮው ዓመት በኢትዮጵያ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች መስተናገዳቸውንና ይህም አምና ከነበረው አንጻር በብዙ እጥፍ እንደሚበልጥ ተናግረዋል።
የኢሚግሬሽን ሪፎርም፣ የአየር መንገድ ስራ፣ የሆቴሎች እና መዳረሻ ቦታዎች ማስፋት፣ የኮሪደር ልማትና ሌሎች ስራዎች ለቱሪስት ፍሰቱ መጨመር ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።
በተያዘው ዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰው አንድነት ፓርክን፣ የወዳጅነት አደባባይን፣ ሳይንስ ሙዚየምንና ብሄራዊ ቤተ መንግስትን መጎብኘቱን በዚህም ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን አመልክተዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት አራቱን ስፍራዎች 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰው መጎበኝቱንም ነው ያነሱት።
በአዲስ አበባ ደረጃ በተከናወኑ ስራዎች የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉንም ገልጸዋል።
ቱሪዝም የአገልግሎት ዘርፍ ቁልፍ ምሰሶ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግስት በዘርፉ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
0 Comments