Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

በክልሉ የወንጀል ምዝገባና የመረጃ አስተዳደር ስርዓት ስራ ማስጀመሪያ ስምምነት ሰነድ ተፈረመ 

ሐረር፣ሰኔ 5/2017(ሐክመኮ):-በሐረሪ ክልል የወንጀል ምዝገባና የመረጃ አስተዳደር ስርዓት ስራ ማስጀመሪያ ስምምነት ሰነድ ተፈረመ።

ስምምነቱ የተደረሰው በሐረሪ ክልል ጠቅላይ አቃቢ ህግ፣በፖሊስ ኮሚሽን እና በክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ መካከል ነው።

የወንጀል ምዝገባና የመረጃ አስተዳደር ስርዓት ሶፍትዌሩ በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የበለጸገ ሲሆን በፍትህ ተቋማት ውስጥ የወንጀል ምርመራና የመረጃ አያያዝ ሂደትን በዘመናዊ መንገድ ለመምራት ያስችላል ተብሏል።

የሐረሪ ክልል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አቶ አዩብ አህመድ ስምምነቱ የወንጀል ምርመራ ስርዓቱን በማዘመን ዜጎች በእውነታ ላይ የተመሠረተ የፍትህ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ብለዋል። 

የፍትህ ተቋማቱ በቀጣይ አገልግሎቱን ስራ ላይ ለማዋል አስፈላጊውን የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ለማሟላት ቀጣይ እቅድ ተይዞ እንደሚሰራም ገልጸዋል። 

የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ረምዚ ሱልጣን በበኩላቸው ስርዓቱ ፍትሐዊ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ያለውን ስራ በማገዝ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀዋል። 

በተለይ ወቅቱ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ ውጤት መታጠቅ ከፍትህ ዘርፉ የሚጠበቅ መሆኑን አክለዋል።

ኮሚሽኑ አሰራሮቹን ወደ ዲጂታል በማሳደግ ረገድ አበረታች ስራዎችን እያከናወነ ይገኛልም ብለዋል።

በክልሉ የሚገኙ ተቋማትን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ዘመኑን የዋጁ እንዲሆኑ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ የገለፁት ደግሞ የክልሉ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ጀማል ኢብራሂም ናቸው። 

በክልሉ ያሉ ተቋማትን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ወደ ስራ መገባቱንና ይህ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የምርምርና እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተማም ስምምነቱ በቴክኖሎጂ የተመራ ዘመናዊ አሰራርን ለማላበስና ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚረዳ ገልጸዋል። 

ዩኒቨርስቲው በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተለያዩ ድጋፍና እገዛዎችን እያደረገ ይገኛል ያሉ ሲሆን በቀጣይም የተሻሉ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ አሰራሮች እንዲኖሩ በማገዝ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish