በክልሉ የህዝቡን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት መነሻ ያደረጉ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ- ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ
ሀረር ሀምሌ 8/2016(ሀክመኮ):- በሀረሪ ክልል የህዝቡን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት መነሻ ያደረጉ ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ እንደሚገኙ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ እንዳሉት የሀረር ከተማን ለነዋሪው ብሎም ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
በተለይ የሀረር ከተማን ጽዱና ውብ ከማድረግ አንፃር በተሰሩ የእግረኛ መንገዶች፣ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ የመንገድ ዳርቻ ማረፊያ መቀመጫዎች፣ የመንገድ የመብራት ተከላ ስራዎች፣ የደህንነት ካሜራዎች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ አንስተዋል።
በቀጣዩ የ2017 የበጀት አመት በከተማው አካባቢ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማጠናከር የገጠሩ አካባቢዎች በፕላን እንዲመሩ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የማህበረሰቡን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎት መነሻ በማድረግ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አክለዋል።
በሌላ በኩል የመንግስት አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣን፣ ውጤታማና ከብልሹ አሰራር የፀዳ እንዲሆን ጠንካራ የዲሲፒሊን ስርአት በመዘርጋት የማህበረሰቡን እርካታ ከፍ የሚያደርጉ ስራዎች እንደሚከናወኑ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።





0 Comments