በክልሉ ኪነ ጥበብ ለአንድነትና ለወል ትርክት ግንባታ ያለውን ድርሻ ለማጎልበት እየተሰራ ነው
በሐረሪ ክልል ኪነ ጥበብ ለብሔራዊ መግባባትና ለወል ትርክት ግንባታ ያለውን ድርሻ ለማጎልበት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የክልሉ የባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው በክልሉ ከሚገኙ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር “ሀገርና ጥበብ፤ ጥበብ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ሃሳብ ውይይት ተካሄደ።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የቢሮው ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ በክልሉ ብሔር-ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፍቅር፣በሰላም እና በአንድነት የሚኖሩበት ባህልና እሴት አለ።
እነዚህ ሀብቶችም ለኪነ ጥበብ ስራ ምቹ አጋጣሚን እንደሚፈጥሩ እሙን ነው ብለዋል።
ኪነ ጥበብ እነዚህን ሀብቶች በመጠቀም የወል ትርክትን ለመገንባት፣ የጋራ መግባባትና አንድነትን የማፅናት ሚናውን ለመወጣት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በክልሉ የተገነቡት የኮሪደር ልማት፣ የጀጎል ዓለም አቀፍ ቅርስ እና የሌሎች ቅርሶች ልማትና ጥበቃ ሥራዎች አሰባሳቢና ገዢ የሆኑ የጥበብ ማህተሞች ያረፈባቸው መሆናቸውን አንስተዋል።
በመሆኑም በተለይም ትውልዱ በተገነቡት የወል ቅርሶችና ልማቶች ውስጥ በጋራ ተሰባስቦ በማውጋት፣ የጋራ መግባባት በመገንባትና አንድነቱን በማፅናት የነገዋን ታላቅ አገር ይረከባል ብለዋል።
እንደ አቶ ተወለዳ ገለፃ፥ዛሬ ከኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጋር እየተካሄደ የሚገኘው ውይይት በክልሉ በየፈርጁ የጋራ ትርክት ለመገንባትና አንድነትን ለማፅናት የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከር መደላድልን ይፈጥራል።
ይበልጥኑ የጥበቡ ባለሙያዎች በአሰባሳቢ ትርክቶች እና በአንድነት ግንባታ ላይ የድርሻቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም መነሳሳትን ይፈጥርላቸዋል ብለዋል።
ቢሮው ከጥበብ ባለሙያዎችና በቡድን ከተሰባሰቡ የጥበብ ባለሙያዎች ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።
በብልፅግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅ/ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጃፈር ሱፊያን በበኩላቸው ዘረፉን መደገፍና ማገዝ የሀገርን እድገትና ልማት መደገፍ እንደሆነ ገልጸዋል።
በመሆኑም ሁሉም የድርሻውን ወስዶ በጋራ በመስራት ውስንነቶችን በማሻሻል ተጠቃሚ ለመሆን መስራት ይገባል ብለዋል።
በመድረኩ የሐረሪ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጃፈር ሱፊያን፣ የክልሉ ባህል ፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽን ጨምሮ በክልሉ በኪነ ጥበብ ዘርፍ የተሰማሩ ሙያተኞችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትና አመራሮች ተገኝተዋል።



0 Comments