በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ ውጤታማ የልማት ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ- የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ
ሀረር ሐምሌ 27/2016(ሀክመኮ)፦ በሀረሪ ክልል የህዝብን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ በየዘርፉ እየተከናወኑ የሚገኙ ውጤታማ የልማት ስራዎችን ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የሀረር ከተማ ስትራቴጂክ የልማት እቅድ ግብረሃይል በሀረር ከተማ እየተተገበሩ የሚገኙ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
በዋናነትም በከተማው እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደር ልማት፣ የከተማ ፅዳትና ውበት እንዲሁም የኢንቨስትመንት ስራዎች በእለቱ ምልከታ ከተደረገባቸው ፕሮጀክቶች ውስጥ ይገኙበታል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በመስክ ምልከታው ወቅት እንዳሉት በክልሉ በመልሶ ልማት፣ በከተማ ፅዳትና ውበት እንዲሁም በኮሪደር ልማት ዘርፍ ውጤታማ ተግባራት እያከናወኑ ይገኛሉ።
በተለይ በፅዳትና ውበት የዕግረኛ መንገዶችን ለዜጎች ምቹ እንዲሆን ለማስቻል የተሰጠው ትኩረት የከተማዋ እድገት በማፋጠን ረገድም ያለው አስተዋፅኦ የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በክልሉ ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው የኮሪደር ልማት የአካባቢን ገፅታ ከመቀየር ባሻገር በልማት ስራው የማህበረሰቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በሚያረጋገጥ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
እየተከናወኑ የሚገኙ ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎችን ከማስቀጠል ጎን ለጎን ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር ከተማው በፕላንና በስርዓት እንዲመራ የማድረግ ተግባርም በላቀ ትኩረትና ቁርጠኝነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አመላክተዋል።
በክልሉ በከተማ ልማት ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ከተማዋና ህዝቡን የሚመጥኑ በተለይ ከነዋሪው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው መሆናቸውንም አንስተዋል።
በሌላ በኩል በሂደት ላይ የሚገኙ የልማት ስራዎችን በተሻለ ፍጥነት በማጠናቀቅ በአዲሱ 2017 በጀት አመት ለማከናወን በዕቅድ የተያዙ ስራዎች ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በመሆኑም እየተሰሩ በሚገኙ የልማት ስራዎችም ማህበረሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ አጠናክሮ ማስቀጠል ወሳኝ መሆኑ ተናግረዋል።



0 Comments