Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

በክልሉ በ 40 አልሚዎች ላይ ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ ኢንቨስትመንት ፍቃድ ስረዛ የሚደርስ እርምጃ ተወስዷል-አቶ ሀምዲ ሰላህዲን

ሀረር፣ጥቅምት 19/2018(ሀክመኮ):-በሀረሪ ክልል በ 40 አልሚዎች ላይ ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ ኢንቨስትመንት ፍቃድ ስረዛ የሚደርስ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ሀምዲ ሰላህዲን ገለፁ።

የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ ሀምዲ ሰላህዲን በሰጡት መግለጫ መሬት ወስደው በውሉ መሰረት ወደ ስራ ባልገቡ፣ግንባታ ባቋረጡና ግንባታቸውን ሳያጠናቅቁ ስራ በጀመሩ በድምሩ 40 አልሚዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ነው የገለፁት።

በዚህም መሰረት እርምጃ ከተወሰደባቸው ባለሐብቶች መካከል 17ቱ በገቡት ውል መሠረት ያላለሙ እና መሬት ተረክበው ወደ ስራ ያልገቡ ናቸው ብለዋል።

18 ቱ ያለ በቂ ምክንያት ግንባታ ያቋረጡና 5 ግንባታቸውን ያላጠናቀቁ ብሎም በከፊል የመስራት ፍቃድ ሳይወስዱ በግንባታው ስራ የጀመሩ አልሚዎች መሆናቸውንም ገልፀዋል።

በዚህም 5 የኢንቨስትመንት ፍቃድ ስረዛ፣18 እገዳ እና 17 ከመጀመሪያ እስከ ጨረሻ ማስጠንቀቂያ በመስጠት እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።

በተለይ ባልተጠናቀቁ ግንባታዎች ላይ ስራ የጀመሩ አልሚዎች ግንባታቸው ባለመጠናቀቁ በዜጎች ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ መሆናቸውን ከግምት በማስገባት እርምጃው መወሰዱን ነው የገለፁት።

የኢንቨስትመንት ፍቃድ የወሰዱ አልሚዎች የስራ እንቅስቃሴን ልዩ ትኩረት በመስጠት በጥብቅ ዲሲፕሊን ከመምራት ጀምሮ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ አልሚዎችን ችግር ለመፍታት በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው።

መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍና ክትትል ባሻገር በኢንቨስትመንት ፍቃድ መሬት ወስደው ወደ ስራ ያልገቡ አልሚዎች ላይም ክትትል በማድረግ ተገቢው እርምጃ የመውሰዱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ሀምዲ ሰላህዲን ገልፀዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish