በክልሉ በተጠናቀቀው የበጀት አመት ከ8 ሺህ 200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል ተፈጥሯል- የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ
በሀረሪ ክልል በተጠናቀቀው የበጀት አመት ከ8 ሺህ 200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የሀረሪ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 3ኛ አመት 6ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ሲሆን በጉባኤም በክልሉ በተጠናቀቀው የበጀት አመት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት በሚመለከት ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ ለምክር ቤቱ ሪፖርት አቅርበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ባቀረቡት ሪፖርትም በ2016 የበጀት አመት በክልሉ በከተማና ገጠር ለሚገኙ ለ9 ሺህ 760 ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ 8286 ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ከተፈጠረው የስራ እድል መካከልም 4938 በከተማ እንዲሁም 3348 ደግሞ በገጠሩ አካባቢ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከብድር ማስመለስ ጋር በተያያዘም ከተዘዋዋሪና ከመደበኛ ብድር 67 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ማስመለስ ስለመቻሉ ጠቁመው 15 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ለ483 ኢንተርፕራይዞች ብድር የማሰራጨት ስራ ተከናውኗል ብለዋል።
የገበያ ዋጋ ንረትን ከማረጋጋት አንፃርም በክልሉ ሶስቱም የገጠር ወረዳዎች አርሶ አደሮች በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ላይ ምርታቸውን እንዲያቀርቡ በማድረግ በአትክልትና ፍራፍሬ ገበያ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ማረጋጋት ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች ወደ ክልሉ እንዲገቡና በቅዳሜና እሁድ ገበያ እንዲያቀርቡ ተደርጓል ብለዋል።
መሰረታዊ ሸቀጦችን ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ተደራሽ ከማድረግ አኳያም 776 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት እንዲሁም 3 ሺህ ኩንታል ስኳር መሰራጨቱን ገልፀዋል።

0 Comments