በክልሉ በቀጣይ 90 ቀናት በየዘርፉ የተገኙ ውጤቶች የበለጠ ለማጎልበት ይሰራል- አቶ ኦርዲን በድሪ
በሀረሪ ክልል በቀጣይ ዘጠና ቀናት በየዘርፉ እየተከናወኑ የሚገኙ ውጤታማ ስራዎች ግለታቸውን ጠብቀው ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ትኩረት ይሰጣል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ተናገሩ
በክልሉ በቀጣይ ዘጠና ቀናት ሊከናወኑ በታቀዱ ስራዎች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይም ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ በቀጣይ ዘጠና ቀናት በተለይም ለገጠር ኮሪደር ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት በከተማውና በጀጎል አለም አቀፍ ቅርስ የተከናወኑ ውጤታማ ስራዎች በገጠር አካባቢዎች ላይ ለመድገም ይሰራል ብለዋል።
በከተማው ያልተጠናቀቁ የኮሪደር ልማት ስራዎችን በአፋጣኝ ማጠናቀቅ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ህብረተሰቡ ፈጣን፣ ፍትሃዊና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል ርብርብ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል።
የግብርና ልማት ስራዎችን ማጠናከርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ውጤታማነት፤ የፅዳትና ውበት ስራዎች ማጎልበት፣ ገቢን ማሳደግና የስራ እድል ፈጠራ የበለጠ ማጎልበት የዘጠና ቀናት ውስጥ የትኩረት አቅጣጫ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኑሮ ውድነት ጫናን ማቃለል ሌላው በዘጠና ቀናቱ ንቅናቄ ከሚሰሩ አንኳር ስራዎች መካከል መሆኑን አመላክተዋል።
የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤታማ ማድረግ እንዲሁም በጤና መድህን አገልግሎት የሚታየው የመድሃኒት አቅርቦት ክፍተት ለመቅረፍና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሳደግ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።
የአምስት ሚሊየን ኮደርስ ስልጠናም አንዱ የርብርብ ማዕከል መሆኑን በማንሳት በክረም በጎ ፍቃድ አገልግሎት አቅመ ደካማ ወገኖችን የመደገፍ ስራ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚህ ቀደም በማህበረሰቡ ዘንድ የተነሱ ቅሬታዎችን ለመቅረፍ መንቀሳቀስ እንደ አንድ ቁልፍ ስራ ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።
በዘጠና ቀናት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የሚደረጉ ጥረቶች ለማሳካት የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።
ለዚህም አመራሩ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ ጌቱ ወዬሳ በበኩላቸው የክልሉ አመራር የተለያዩ የልማት ስራዎችን በጥራት እና በአጠረ ጊዜ የማሳካት ቅንጅታዊ ብቃቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን በማንሳት በዘጠና ቀናት የሚሰሩ ስራዎችም የፓርቲ እና የመንግሥት አቅሞችን በማስተባበር ማሳካት በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል።
በንቅናቄው መድረክ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ሱልጣን እብደሰላም ፣ የሀረሪ ብሄራዊ ጉባኤ አፈ ጉባኤ አቶ ሙህየዲን አህመድ ፣ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳን ጨምሮ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ ሮዛ ኡመርን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

0 Comments