በክልሉ በቀጣዩ 3 ወራት 25 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ ለማከናወን እየተሰራ ነው -አቶ ሙክታር ሳሊህ
በሀረሪ ክልል በቀጣዩ 3 ወራት 25 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ ለማከናወን እየተሰራ እንደሚገኝ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር መዓረግ የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ ገለፁ።
የኮሪደር ልማት ኢንሼቲቩ የሀረር ከተማን ገፅታ የቀየረ እና የክልሉን የወደፊት ዕድገት ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተከናወነ ዘመን ተሻጋሪ የልማት ስራ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር መዓረግ የሀረሪ ክልል ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ ገልፀዋል።
አቶ ሙክታር ሳሊህ እንደገለፁት በክልሉ በአንደኛው ዙር በተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በተለይ በአለም አቀፉ የጁገል ቅርስ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ ቅርሱን ተጋርጦበት ከነበረው አደጋ የታደገ እና ህልውናውን ያስቀጠለ እንደነበር አንስተዋል።
ሀረር በአለም ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው ሁለት ቅርሶች እንዱ የሆነው ህያው የጁገል ቅርስ ለነዋሪዎች ብሎም ጎብኚዎች በማይመች ሁኔታ ላይ እንደነበርም አቶ ሙክታር ሳሊህ አስታውሰዋል።
ቅርሱን ከአደጋ ለመታደግ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሪነት ማህበረሰቡን በማስተባበር በተሰራው የኮሪደር ልማት ስራ ካለ ምንም የመንግስት ወጪ ቅርሱን መልሶ በማልማት ለነዋሪው ብሎም ጎብኚዎች ምቹ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።
ክልሉ አንድ የቱሪዝም መዳረሻ እንደመሆኑ በክልሉ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች የቱሪዝም ፍሰቱን ከማሳደግ ባለፍ የቱሪስቶችን ቆይታ በማርዘም ዘርፉ ማስግኘት የሚገባውን ጥቅም ለማስገኘት የሚረዳ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በተለይ በክልሉ የመናፈሻ እና ማረፊያ ስፍራዎች ውስንነት እንደነበር የገለፁት አቶ ሙክታር በተከናወነው የኮሪደር ልማት የኑር ፕላዛ መናፈሻን ጨምሮ ሰዎች የሚያርፉባቸው እና የሚዝናኑባቸው ስፍራዎች መፈጠራቸውን አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል የኮሪደር ልማት ስራው በምሽት ጭምር እየተከናወነ የሚገኝ የክልሉን የስራ ባህል የቀየረ እና ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በመጨረስ የይቻላል መንፈስን የፈጠረ መሆኑን አክለዋል።
ስራው የክልሉን ማህበረሰብ የልማቱ ባለቤት አድርጎ በማሳተፍ ልምድ የተወሰደበት እንደሆነም አስገንዝበዋል።
ማህበረሰቡን በማሳተፍ በተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ የተገኙ ልምዶችን ቀምሮ ወደ ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ መገባቱንም አስገንዝበዋል።
በዚህም መሰረት በቀጣዩ 3 ወራት ብቻ በከተማ እና በገጠር ወረዳዎች 25 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራዎችን ለማከናወን ዕቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን አስታውቀዋል።
አሁን ባለበት ደረጃም ስራውን ለማከናወን የወሰን ማስከበር ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ማህበረሰቡ ለልማቱ እያደረገው ያለው ትብብር ለስራው ምቹ ሁኔታን መፍጠሩንም ገልፀዋል።
የኮሪደር ልማቱ የኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው በመጠቆም የክልሉ መንግስት ግብረሃል በማቋቋም የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝም አቶ ሙክታር ሳሊህ ገልጸዋል።
0 Comments