በከተማ ልማት ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስፋት በትኩረት ይሰራል-አቶ ኦርዲን በድሪ
ሀረር ሀምሌ 22/2016(ሀከመኮ):- በ2016 በጀት ዓመት በከተማ ልማት ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስፋት በትኩረት እንደሚሰራ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ የሀረር ከተማን ዕስትራቴጂክ ዕቅድ ለመምራት ከተዋቀረው ግብረሀይል ጋር በክልሉ ተጀምረው በሂደት ላይ በሚገኙ እና በበጀት ዓመቱ ተግባራዊ በሚደረጉ አዲስ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ መክረዋል።
በምክክሩ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለፁት የማህረሰቡን የረጅም ዓመት የልማት ጥያቄ ለመመለስ በ2016 በጀት ዓመት በክልሉ በመሰረተ ልማት ፣በከተማ ውበት እና ፅዳት ስራ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልፀዋል።
በተለይ በበጀት ዓመቱ በኮሪደር ልማት ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎች ማህበረሰቡን ቀጥተኛ ተጠቃሚ የሚያደርጉ እና የማህበረሰቡን ይሁንታ ያገኙ ሆናቸውን ገልፀዋል።
በመሆኑም የተጀመሩ ስራዎቸን በፍጥነት በማጠናቀቀ በቀጣዩ የ2017 በጀት ዓመት ተጨማሪ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ለማስጀመር ትኩረት ተሰቶ ይሰራል ብለዋል።
በከተማ ልማት ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶችን በማስፋት ለኑሮ ብሎም ለጎብኚዎች የተመቸች ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አዳዲስ የገበያ ሼዶችን በመገንባት በመንገድ ላይ የሚካሄዱ ስርዓት አልባ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ስርዓት ለማስያዝ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
በከተማ ውበት እና ፅዳት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ በመስክ ምልከታ የፕሮጀክቶች አፈፃፀምን ክትትል እና ድጋፍ እደሚደረግም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በትራነስፖርት ዘርፍ በተለይ የመንጃ ፍቃድ ፣ ቦሎ እና ታርጋ ቁጥጥርን በማጠናከር በህገ ወጦች ላይ ጠንከር ያለ አስተማሪ የዕርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተስተዋለውን መነቃቃትም እንዲጎለብት አስፈላጊው የድጋፍ እና ክትትል ስራ እንደሚሰራም ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገልፀዋል።



0 Comments