በኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ወደ ስራ ያልገቡ አልሚዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል-ርዕሰ መስተዳድር:-አቶ ኦርዲን በድሪ
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በኢንቨስትመንት መሬት ወስደው ወደ ስራ ያልገቡ አልሚዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ አስቀመጡ።
የሀረሪ ክልል ኢንቨስትመንት ቦርዱ የክልሉን ኢንቨስትመንት ማዕድንና ኢነርጂ ፅ/ቤት አንደኛ ሩብ ዓመት የስራ አፈፃፀም ገምግሟል።
ፅ/ቤቱ ለቦርዱ ባቀረበው ሪፖርት በክልሉ በኢንቨስትመንት ፍቃድ መሬት ወስደው ወደ ስራ ባልገቡ አልሚዎች ላይ ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ ኢንቨስትመንት ፍቃድ ስረዛ እርምጃ መወሰዱን አመላክቷል።
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በወቅቱ እንደገለፁት የኢንቨስትመንት ፍቃድ የወሰዱ አልሚዎች የስራ እንቅስቃሴን ልዩ ትኩረት በመስጠት በጥብቅ ዲሲፕሊን መምራት ይገባል።
መንግስት በክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሰማሩ አልሚዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በዘርፉ አልሚዎች ላይ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት ይሰራል ብለዋል።
በኢንቨስትመንት ፍቃድ መሬት ወስደው ወደ ስራ ያልገቡ አልሚዎች ላይም ክትትል በማድረግ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ርዕሰ መስተዳድሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
0 Comments