Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

በሐረር ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ማህበራዊ ችግሮችን እየቀረፈ ነው – ነዋሪዎች

በሐረር ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ከመቀየርና የመዝናኛ ስፍራዎችን ከማጎናፀፉ ባለፈ ያጋጥሙ የነበሩ ማህበራዊ ችግሮችን መቅረፉን የከተማው ነዋሪዎች ተናገሩ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ አብዱ ኡመር በኮሪደር ልማቱ በተጨባጭ የተመለከትነው ከተማዋን መለወጡንና ነዋሪውን መጥቀሙን ነው ብለዋል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት የኮሪደር ልማቱ ነፋሻማ አየር እንድናገኝ፣ አረንጓዴ ስፍራ እንድንጎናፀፍ በርካታ እድሎችን አበርክቶልናል ሲሉም ገልፀዋል። 

መምህር ግርማ አየለ የሐረር ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ለ53 ዓመታት ብስክሌት አሽከርክረዋል።

ቀደም ሲል በከተማው የነበረው የአስፓልት መንገድ ለሳይክል ማሽከርከር ምቹ ባለመሆኑ ከተሽከርካሪ እና ከእግረኛ ጋር በመጋፋትና አደጋ ይደርስብኛል በሚል ስሜት ብስክሌት በስጋት እንደሚያሽከረክሩ ያስታውሳሉ።

በአሁኑ ወቅት በከተማው የተከናወነው የኮሪደር ልማት የብስክሌት፣ የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገድ በተለያየ ሁኔታ መገንባቱ ይታይ የነበረውን ስጋት ሙሉ ለሙሉ የቀረፈ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማቱ የከተማውን ገጽታ የቀየረና ለእግረኛና ለተሽከርካሪ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ይታዩ የነበሩ ማህበራዊ ችግሮችን የቀረፈ ነው ብለዋል።

በከተማው የተከናወነው የኮሪደር ልማት እጅግ አስደማሚና ህብረተሰቡን እየጠቀመ ያለ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ከፈለኝ ደቻሣ ናቸው። 

በተለይ የእግረኛና የተሸከርካሪ መንገድ ተለያይቶ መገንባቱ ቀደም ሲል ያጋጥሙ የነበሩ የትራፊክ አደጋዎችን በመቀነስ ልጆቻችንን በነጻነት ወደ ትምህርት ቤት እንድንልክ አስችሎናል ብለዋል።

የ12ኛ ክፍል ተማሪ ሃያት ሚፍታህ እንዳለችው የኮሪደር ልማቱ ከተማዋን ውብና ማራኪ አድርጎልናል። 

በተለይም እኛ ተማሪዎች የመዝናኛ ስፍራዎችን እንድናገኝ እድል ፈጥሮልናል፤ በዚህም እጅግ ደስተኛ ነኝ ብላለች ሲል ኢዜአ ዘግባል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish