Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

በሐረሪ ክልል 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ኢንቨስትመንት ላስመዘገቡ አልሚዎች ከ 56 ሺ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ተላልፎ እንዲሰጥ ውሳኔ ተላለፈ

ሐረር፤ግንቦት 1/2017(ሐክመኮ):-የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ኢንቨስትመንት ላስመዘገቡ አልሚዎች የሚውል ከ 56 ሺ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ተላልፎ እንዲሰጥ ውሳኔ አሳለፈ።

መስተዳድር ምክር ቤቱ ለአልሚዎች በምደባ እንዲሰጥ በቀረበው 56 ሺ 494 ካሬ ሜትር መሬት ላይ በመምከር ነው የቀረበው መሬት ለአልሚዎች እንዲተላለፍ ውሳኔ ያሳለፈው።

መሬት በምደባ እንዲሰጣቸው ውሳኔ የተላለፈው 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ኢንቨስትመንት ላስመዘገቡ አልሚዎች መሆኑም ተመላክቷል።

መሬቱ ለትራንስፖርት አገልግሎት፤ለአግሮ ኢንዱስትሪና ማኑፋክቸሪንግ፤ለሆቴል እና ሪዞርት፤ለቅይጥ አገልግሎት፤ለሆስፒታል እና ጤና አገልግሎቶች የሚውል መሆኑም ነው የተገለፀው።

በመሬት ምደባው ወቅት ለክልሉ ልዩ ፋይዳ አላቸው ተብለው በተለዩ የማኑፋክቸሪንግ፤በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለሚሰማሩ አልሚዎች ብሎም የመልሶ ልማት ለሚከናወንባቸው አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ተሰቷል።

አልሚዎችን በግልጽ መስፈርት በመለየት በልዩ ሁኔታ መሬት እንዲሰጥ መስተዳድር ምክር ቤቱ  ውሳኔ ያሳለፈ ሲሆን አልሚዎች የወሰዱትን መሬት በአፋጣኝ በማልማት ለተፈለገው ዓላማ እንዲውል ወደ ስራ እንዲገቡም አሳስቧል።

በምደባ እንዲተላለፉ የውሳኔ ሀሳብ ከተሰጠበት ከ 56 ሺ  ካሬ ሜትር በላይ መሬት ውስጥ 38 ሺ  464 ካሬ የሚሆነው ከመሬት ባንክ እንዲሁም 18 ሺ 10 ካሬ ሜትሩ በመልሶ ልማት የሚከናወን መሆኑ ተመላክቷል።

በሚከናወኑ የመልሶ ልማቶች ላይ በራስ አገዝ ለሚያለሙ ዜጎች ቅድሚያ የሚሰጥ ይሆናል።

በተለይ በቅይጥ የተለዩ አልሚዎች የግንባታቸውን የታችኛው ክፍል ለስራ በማዋል የላይኛውን ክፍል ለመኖሪያ ቤት እንዲያውሉ የሚደረግ ሲሆን የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር በመጠኑ ለመቅረፍ የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።

መሬት በምደባ የተሰጣቸው አልሚዎች በግዜ ወደ ስራ እንዲገቡ በተለይ ካሁን ቀደም የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ስራ ያልጀመሩ አልሚዎች ስራቸውን እንዲያጠናቅቁ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ይደረጋል።

የኢንቨስትመንት ቦርዱም መሬት የወሰዱ አልሚዎች የወሰዱትን መሬት በግዜ ወደ ስራ በመግባት ለታለመለት አላማ እንዲያዉሉ የክትትል ስራ እንዲያከናውን አቅጣጫ ተቀምጧል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish