በሀረር ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የጤና ኮሪደር የሜዲካል ቱሪዝሙን ይበልጥ የሚያጎለብት ነው-ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
ሀረር ሰኔ 10/2016(ሀክመኮ) በሀረር ከተማ እየገነባ የሚገኘው የጤና ኮሪደር የሜዲካል ቱሪዝሙን ይበልጥ እንዲጎለብት የሚያደርግ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በሀረር ከተማ እየተገነባ የሚገኝውን የጤና ኮሪደር ልማት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በመስክ ምልከታው ወቅትም ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በሀረር ከተማ ከአጂፕ እስከ ደከር የጤና ኮሪደር በመገንባት በክልሉ ያለውን የሜዲካል ቱሪዝም አሁን ካለበት በተሻለ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገለፁ።
በክልሉ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የጤና ኮሪደር ልማት መንገዱን ቀድሞ ከነበረበት 7 ሜትር ስፋት ወደ 30 ሜትር በማስፋት ግንባታው እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል።
መንገዱ የተሽከርካሪ ፤ብስክሌት እና የእግረኛ መንገድን በማካተት የእስማርት ሲቲ ሞቢሊቲ ፅንስ ሀሳብን ባማከለ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የኮሪደር ልማት ስራው በአካባቢው የሚገኙ የተለያዩ የግል እና የመንግስት የጤና ተቋማትን እርስ በእርስ የሚያገናኝ መሆኑንም አክለዋል።
በቀጣይም በጤናው ዘርፍ ኢንቨስት የሚያደርጉ ባለሀብቶች በኮሪደሩ ላይ የመስሪያ ቦታ እንደሚመቻችላቸው በመግለፅ።
ሀረር በታሪክ አጋጣሚ የምስራቅ ኢትዮጵያ ዋና ከተማ እንደነበረች ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በአሁኑ ሰዓት ከምስራቁ የአገሪቱ ክፍል ብሎም እንደ ሶማሊያ ካሉ ጎረቤት አገራት ሰዎች ህክምና ለማግኘት ወደ ሀረር ከተማ እንደሚመጡ ገልፀዋል።
የጤና ኮሪደር ልማቱ በርካታ የጤና ተቋማትን ያቀፈ መሆኑ ዜጎች አማራጭ ኖሯቸው ለተጨማሪ ወጪ እና እንግልት ሳይዳረጉ የፈለጉትን አገልግሎት በአንድ አካባቢ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል ኮሪደሩ በጤና ተቋማት መካከል ጤናማ የሆነ ውድድር እና ትብብር እንዲኖር በማስቻል የጤና ተቋማቱ የተሻለ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ከማድረግ አኳያ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ነው የገለፁት።
አሁን ላይ በክልሉ የጤና ኮሪደር ልማትን ዕውን ለማድረግ መሰረት እየተጣለ ሲሆን በቀጣይ አስር አመታት በጤና ቱሪዝም ዘርፍ የተሻለ ስራ በመስራት የአካባቢውን ኢኮኖሚ በመቀየር ለነዋሪዎች የተሻለ የስራ ዕድል የሚፈጠርበት እንደሚሆን ገልፀዋል።
የሜዲካል ቱሪዝም ሀረር ካሏት የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች አንዱ መሆኑን በመጠቆም የኮሪደር ልማቱ የሜዲካል ቱሪዝሙን ይበልጥ የሚያነቃቃ መሆኑን ገልፀዋል።




0 Comments