Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

በሀረር ከተማ ህዝብን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወኑ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የከተማው ማዘጋጃ ቤት አስታወቀ

ሀረር ከተማን ውበትና ፅዳት በማስጠበቅ ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎች ምቹ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የከተማው ማዘጋጃ ቤት አስታውቋል።

የሀረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ኢሊያስ ዩኒስ ማዘጋጃ ቤቱ እየተከናወኑ ስለሚገኙ ዋና ዋና ተግባራት በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ቀደም ሲል በከተማው ከፅዳት ጋር በተያያዘ ሰፊ ክፍተት ሲስተዋል መቆየቱን ገልፀው ችግሩን ለመቅረፍም አዳዲስ የአሰራር ስርዓቶች በመዘርጋት ከተማዋን በሚመጥናት ደረጃ ፅዱና ውብ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ለዚህም በበጀት አመቱ የከተማውን ማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማጎልበት ህዝቡን ያሳተፈ የከተማ ውበትና ፅዳትን የማስጠበቅ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

ሀረር ከተማን ለነዋሪዎቿ የተመቸች፣ ጽዱና ዘመናዊ ከተማ የማድረግ ውጥን በመያዝ የኮሪደር ልማትም ስራዎች በላቀ ቅንጅትና ርብርብ በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል።

በኮሪደር ልማቱ የመንገድ አውታሮችን የማስፋፋት፣ ዘመናዊ የመብራት ዝርጋታ፣ የአረንጓዴ ልማት፣ ምቹ የእግረኛ እና ብስክሌት መንገድ ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በከተማዋ የሚስተዋለውን ህገወጥ የመንገድ ዳር ንግድ እና ህገወጥ የቤት ግንባታን በመከላከል ረገድም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።

በከተማው እየተስተዋሉ የሚገኙ የደንብ መተላለፎችንና ተያያዥ ሕገ-ወጥ ተግባራትን በዘላቂነት ለመከላከል ብሎም እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ደንብ በክልሉ መስተዳድር ም/ቤት ፀድቆ ወደ ስራ በተጠናከረ ሁኔታ መገባቱን ገልፀዋል፡።

ከአረንጓዴ ልማት ስራዎች ጋር በተያያዘም ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ ከተማዋን ውብና ሳቢ የማድረግ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ደረቅ ቆሻሻን የመሰብሰብ፣ የመለየትና ጥቅም ላይ እንዲውል የማዋል ስራዎችም የላቀ ትኩረት በመስጠት እየተሰራና በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ዙሪያ ህብረተሰብ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አረንጓዴ ስፍራዎችን በመለየት እንዲለሙና እንዲጠበቁ የማድረግ ስራ በትኩረት ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡም እየተከናወኑ በሚገኙ ስራዎች ድጋፉን በማጠናከር ሀረር ታሪኳንና ስልጣኔዋን በሚጥን ደረጃ ውብ፣ ፅዱና ስማርት ከተማ ለማድረግ እየተከናወኑ በሚገኙ ስራዎች ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

en_USEnglish