በሀረሪ ክልል በዘንድሮ ዓመት በበጋ መስኖ 4 ሺህ 851 ሄክታር መሬት ይለማል
ሀረር፤ ጥቅምት 23/2018(ሀክመኮ)፦ በሐረሪ ክልል በዘንድሮ የበጋ መስኖ 4ሺህ 851 ሄክታር መሬት እንደሚለማ የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡
የቢሮው ምክትል ሃላፊ ነስረዲን አህመድ እንዳሉት፥ በክልሉ በዘንድሮ የበጋ ወቅት መስኖ እርሻ ያሉትን የውሃ አማራጮች በሙሉ በመጠቀም 4ሺህ 851 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
በመስኖ የሚለማውም ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመን፣ ቃሪያ፣ ካሮትና ሌሎች የአትክልትና የሰብል ዓይነት መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሁለት ዙር በመስኖ ከሚለማው መሬት በድምሩ ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ዘንድሮ በመስኖ የሚለማው መሬት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ402 ሄክታር መሬት ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል።
ለመስኖ ልማቱ ምርጥ ዘርና ሌሎች የምርት ማሳደጊያ ግብዓት በቢሮውና በወረዳዎች መሟላቱን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ለመስኖ ልማቱ የሚያገለግል ተጨማሪ 200 የውሃ መሳቢያ ሞተሮችና ዲናሞ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱንም ተናግረዋል።
በየደረጃው ለሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችና የልማት ጣቢያ ሰራተኞች አስፈላጊው የቴክኒክና የሙያ ስልጠና መሰጠቱንም ገልጸዋል።
በክልሉ ባለፈው ተመሳሳይ ዓመት 4ሺህ 449 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ መልማቱን ጠቅሰዋል።
የመስኖ ልማቱ በተለይም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት አርሶ አደሩንና የከተማ ነዋሪውን በቀጥታ በማገናኘት የገበያ መረጋጋት እየፈጠረ እንደሚገኝና ህብረተሰቡም ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻሉን አመላክተዋል።

0 Comments